ቀጥታ፡

የኦሮሚያ ክልል ዳያስፖራ አባላት በክልሉ የመንግስት ምስረታ ሂደት ላይ ለመገኘት አዲስ አበባ ገቡ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14/2014 ( ኢዜአ) የኦሮሚያ ክልል ዳያስፖራ አባላት በነገው እለት በሚካሄደው የክልሉ የመንግስት ምስረታ ሂደት ላይ ለመገኘት አዲስ አበባ ገብተዋል።

የዳያስፖራ አባላቱ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የክልሉ የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

በዚህ መርሃ ግብር ላይ ለመገኘት አዲስ አበባ የገቡት ዳያስፖራዎቹ በፖለቲካ ሳቢያ ለአርባ ዓመታት ገደማ ከአገራቸው ርቀው የቆዩ መሆናቸው ተገልጿል።

የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩንኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ፤ የዳያስፖራ አባላቱ በአገሪቷ ለውጥ እንዲመጣ በተለያዩ መንገዶች ሲታገሉ የቆዩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በያሉበት አገር የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ውስጥ ተቀላቅለው ሲሳተፉና ሲመሩ መቆየታቸውን አስታውሰው ነገ በሚከናወነው የክልሉ መንግስት ምስረታ ላይ እንዲገኙ መጋበዛቸውን ጠቁመዋል።

በቀጣይም በርካታ የክልሉ ተወላጅ የዳያስፖራ አባላት እንደሚመጡ ይጠበቃል ብለዋል።

የዳያስፖራ አባላት ወደ አገራቸው መምጣት ቅድሚያ ራሳቸው የጠራ ግንዛቤ እንዲይዙ የሚያደርግና ለሌሎችም ትክክለኛ መረጃ የሚሰጥ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በዴሞክራሲ፣ በልማት፣ በመልካም አስተዳደር ተለውጣ ማየት የማይፈልግ ዜጋ ባለመኖሩ ሁሉም ዜጋ አንድ አገር እንዳለው ለማስታወስ ያህልም ነው ይላሉ።

የዳያስፖራ አባላቱ በበኩላቸው "በኢትዮጵያ ይሆናል ብለው ያልጠበቁት ነገር በመሆኑ" ወደ አገራቸው መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ለሁሉም ዜጎቿ የተመቸች ኢትዮጵያ እውን እንድትሆን በተለያየ መልኩ ሲታገሉ መቆየታቸውን ጠቅሰው አሁን ወደዛ የሚወስድ መንገድ መጀመሩን አንስተዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ዶክተር ጀማል ሀሰን እና ዶክተር ማርቆስ ቤኩቶ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው አምባገነን መንግስት ምክንያት ወደ አገራቸው መጥተው እንደማያውቁ ተናግረዋል።

አሁን ግን ለብሔር ብሔረሰቦቿ የምትመች ኢትዮጵያ እየተመሰረተች መሆኑን የሚያሳይ ተስፋ በመኖሩ መምጣታቸውን ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም