ቀጥታ፡

መንግስትና ህብረተሰቡ የሚያደርግላቸው ድጋፍ በፍትሃዊነት እንዲደርሳቸው ተፈናቃዮች ጠየቁ

ደሴ፤ መስከረም 14/2014 (ኢዜአ) በመንግስትና በህብረተሰቡ የሚደረግላቸው ድጋፍ በፍትሃዊነት እየደረሳቸው ባለመሆኑ እንዲስተካከል በደሴ ከተማ ጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ተፈናቃዮች ጠየቁ።

የጅማ ዩኒቨርሲቲና ዶክተር አረጋ ይርዳው በህወሓት የሽብር ቡድን ተፈናቅለው ደሴ ከተማ ለተጠለሉ ተፈናቃዮች የእለት ደራሽ ምግብና ቁሳቁስ ዛሬ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

በዚህ ወቅት ከተፈናቃዮች መካከል አቶ የሱፍ አደም ለኢዜአ እንዳሉት፤ በአሸባሪው ህወሃት ቡድን ከሐራ ከተማ ተፈናቅለው የእለት ደራሽ ምግብ እንዲጠብቁ ተገደዋል።

''ችግራችንን የተረዱ ግለሰቦች፣ ተቋማትና መንግስት የእለት ደራሽ ምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ እያደረጉልን ቢሆንም  እርዳታው በፍትሃዊ መንገድ እየደረሰን አይደለም'' ብለዋል።

የሚመለከተው አካል ችግሩን በአስቸኳይ እንዲፈታ የጠየቁት አቶ የሱፍ ቅድሚያ ማግኘት የሚጠበቅባቸው ሴቶችና አዛውንቶች እያሉ ጉልበተኞች ከቤተሰቦቻቸው ቁጥር በላይ በተደጋጋሚ በመውሰድ ጭምር የእርዳታው ፍትሃዊነት እንዲዛባ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

ወይዘሮ ዘውዴ በላይ በበኩላቸው፤  በአሸባሪው የህወሓት ቡድን በግፍ ብንፈናቀልም የኢትዮጵያ ህዝብ ባሳየን አጋርነትና አብሮነት ተደስተናል፤ ተስፋም ሰንቀናል ብለዋል፡፡

በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ግለሰቦችና ተቋማት ርቀት ሳይገድባቸው እኛን ለመርዳት ጥረት ከማድረጋቸው  ባለፈ በአካል እየመጡ መጎብኘታው ብርታት እንደሆናቸው ገልጸዋል።

ሆኖም  እየመጣ ያለው ድጋፍ በአግባቡ እየደረሰን ባለመሆኑ  አዝነናል ብለዋል።

መንግስትና ባለድርሻ አካላት ድጋፉ በትክክል እንዲደርስ ክትትልና ቁጥጥር እንዲደርሳቸው ጠይቀዋል።

አንድ ወረዳ ላይ የተመዘገበ፤  ሌላ ወረዳ ላይ ተመዝግቦ ተጨማሪ ድጋፍ ለማግኘት መሞከሩ የምንገኝበትን ክፉ ቀን ከግምት ውስጥ ያላስገባ  ስግብግብነት በመሆኑ መቆም አለበት ብለዋል፡፡

 የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወልደትንሳኤ መኮንን ፤  በተለያዩ አካላት ለተፈናቃዮች ተብለው የሚመጡ ድጋፎች ስርጭት ክፍተት እንዳለበት በግምገማ ማረጋገጣቸውን ጠቁመው፤ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል እየተሰራን መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ቅድሚያ መሰጠት ያለባቸውም ቅድሚያ እንዲያገኙ ፣ድጋፉ ለተፈናቃዮች በቤተሰባቸው ቁጥር ልክ በትክክል እንዲደርስ ለማድረግ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ መጀመሩን አስታውቀዋል።

የተፈናቃዮች ቁጥር መብዛትና የቅንጅት ክፍተት መኖሩ አሰራሩን ፍትሃዊ እንዳይሆን አድርጎታል ብለዋል።

ድጋፉም ደሴ ከተማ ላይ ለተጠለሉት ብቻ ሳይሆን ከቀያቸው ላልወጡትና ጫካ ውስጥ ለሚኖሩትም  ባሉበት ቦታ በፍትሃዊነት ለማድረስ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ድጋፍ ያደረጉት ዶክተር አረጋ ይርዳው በበኩላቸው፤ ቤተሰቦቻቸውን አስተባብረው ከሞቀ ቤታቸው በግፍ ለተፈናቀሉ ዜጎች የምግብ እህልና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ከድጋፉ መካከል 500 የፕላስቲክ ኩባያ፣200 ብርድ ልብስ፣160  ምንጣፍ፣ 20 ኩንታል ማካሮኒና ሩዝ፣ብረት ድስትና ሌሎች የምግብ  ማዘጋጃ  ቁሳቁሶች ይገኙበታል፡፡

በተመሳሳይ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ተወካይ አቶ ወልዱ አሰፋ፤  2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብ እህልና ምግብ ነክ ያልሆነ ቁሰቁስ በወሎ ዩኒቨርሲቲ በኩል ለተፈናቃዮች  እንዲደረሳቸው  ማምጣታቸውን አስታውቀዋል።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች በፈጸመው የግፍ ወረራ የተፈናቀሉ ወገኖችን ችግር በመረዳት መንግስት ፣ የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች  ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በማመቻቸት እያቀረቡ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም