የዜጎች ሞት፣ መፈናቀልና አለመረጋጋት በአፋጣኝ መፍትሄ ሊያገኝ ይገባል - ኢሶዴፓ - ኢዜአ አማርኛ
የዜጎች ሞት፣ መፈናቀልና አለመረጋጋት በአፋጣኝ መፍትሄ ሊያገኝ ይገባል - ኢሶዴፓ
አዲስ አበባ ነሀሴ 9/2010 "በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች እየተከሰተ ያለው የዜጎች ሞት፣ መፈናቀልና አለመረጋጋት አፋጣኝ መፍትሄ ይበጅለት" ሲል የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ጥሪ አቀረበ። የፓርቲው ኃላፊዎች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል። የፓርቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ''ከብሄራዊ ክልላቸው ውጪ የሚኖሩ ዜጎች መብት ያለመከበር ጉዳይ የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት እየተፈታተነ ያለ ትልቅ አደጋ ነው፤'' ሲሉ አስጠንቅቀዋል። በአሁኑ ወቅት በየአካባቢው የሚስተዋለው ይህ ተግባር "ኢትዮጵያዊያን በመረጡት ቦታ ተዘዋውረው መኖር፣ ሀብትና ንብረት ማፍራት ይችላሉ" የሚለውን ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌን የሚጥስ መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰሩ አስተማማኝ ሠላም ለማምጣት ከተፈለገ ጉዳዩ ዘላቂ መፍትሄ ሊበጅለት እንደሚገባ አሳስበዋል። " 'ከክልላችን ውጡ!' በሚል የሚፈጸመው ይህ ፀረ-ህገ መንግስት ሁኔታ የህይወት መጥፋትን፣ የንብረት ውድመትን፣ መፈናቀልንና ስደትን ጨምሮ ንፁሃን ዜጎችን ለተለያዩ መከራዎች እየዳረገ ያለ እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ ተግባር ነው'' ሲሉ ፕሮፌሰር በየነ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እየሰጡ ከሚገኙት የተስፋ ቃል፣ እየወሰዷቸው ካሉት ገንቢ እርምጃዎችና የዳያስፖራ ማህበረሰብን በማነጋገር የፈጠሩትን የማቀራረብ ተግባር በጎ ጅምር እድርገው እንደሚመለከቱት ገልፀዋል። ''እንዲያም ሆኖ ግን የተወሰኑ የብሄር ተወላጆችን ኢላማ በማድረግ የሚፈጠሩ ግጭቶችን፣ ጠባብ ዓላማዎችን ለማሳካት የሚፈልጉ ኃይሎች በየቦታው የሚገኙ ስራ አጥ ወጣቶችን በማደራጀት ለሚፈጽሙት የጥፋት ተግባር አፋጣኝ እርምጃ አለመወሰዱ ተገቢ አይደለም'' ብለዋል። በተለይ ደግሞ ከአከላልና ብሄራዊ የአስተዳደር እርከን እንዲሰጥ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች እንደዚሁም ከብሄረሰባዊ ማንነት ጋር በተያያዘ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ህገ መንግስቱን መሰረት ያደረገ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል ሲሉም አመልክተዋል። በሌላ በኩል ገዢው ፓርቲ ከሁለት ዓመት በኋላ ለሚደረገው ምርጫ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሥራ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ቢሰራ የተሻለ እንደሚሆንም አክለዋል። የፓርቲው ምክትል ዋና ጸሀፊ ወይዘሮ ራሄል ቦፌ በበኩላቸው በአገሪቷ ለሚታየው አለመረጋጋት የተሿሚዎች አቅም ማነስ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰው ብቃት ባለውና በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ባለው አመራር መተካት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።