ዪኒሴፍ በኢትዮጵያ ለድንገተኛ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ መስጠትና የአቅም ግንባታ ልምድ ያጋራል - ኢዜአ አማርኛ
ዪኒሴፍ በኢትዮጵያ ለድንገተኛ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ መስጠትና የአቅም ግንባታ ልምድ ያጋራል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) ዪኒሴፍ በኢትዮጵያ ለድንገተኛ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ መስጠትና የአቅም ግንባታ ልምድ እንደሚያጋራ የድርጅቱ የመድሃኒት አቅርቦት ዘርፍ ዳይሬክተር ኢትላቫ ካድሊ ገለጹ።
ዳይሬክተሯ የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት ኤጂንሲን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸው ወቅት የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ የመድሃኒት ተደራሽነትን በሚፈለገው ጊዜና በተመጣጣኝ ዋጋ ለማድረግ በአጭርና በረጅም ጊዜ ሊሰራቸው ያሰባቸው ዕቅዶች አድንቀዋል።
ዕቅዱን ለማሳካትና የአቅርቦት ሰንሰለቱን ለማዘመን በሚሰራቸው ስራዎች ዩኒሴፍ ከኤጀንሲው ጋር በትብብር እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
በተለይ ለድንገተኛ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ መስጠትና በሰው ሃይል አቅም ግንባታ ልምድ በማካፈል ኤጂንሲው ኅብረተሰቡን ለማገልገል ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚግዙ ነው የተናገሩት።
ለድንገተኛ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ በመስጠት በኩል የዩኒሴፍን ልምድና ተሞክሮዎች ለማካፈል ዝግጁ መሆናቸውንም ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ ኤጄንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋአለም አድራሮ ኤጄንሲው በቀጣይ 10 ዓመት በአገሪቷ ትልቅ የመድሃኒት ማከማቻ ማዕከል ለመገንባት ማቀዱን ገልጸዋል።
ዳይሬክተሯ የመድሃኒት ማከማቻ ግንባታውን ጨምሮ የአቅርቦትና ስርጭት ልምዳቸውን ለማካፈል ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋልም ብለዋል።
የድንገተኛ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ አሰጣጥ ልምዳቸውን ለማካፈል ቃል መግባታቸውን አስታውሰው፤ የዳይሬክተሯ ጉብኝት ለኤጂንሲው ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል።
ዩኒሴፍ በተለያዩ ምክንያቶች ለምግብ እጥረት ለተዳረጉ እናቶችና ህጻናት እያደረገ ላለው የአልሚ ምግቦች ድጋፍም አመስግነዋል።