ማህበሩ በሴቶች ላይ የሚፈጸም በቡድን አስገድዶ የመድፈርና የአሲድ ጥቃት አሳስቦኛል አለ - ኢዜአ አማርኛ
ማህበሩ በሴቶች ላይ የሚፈጸም በቡድን አስገድዶ የመድፈርና የአሲድ ጥቃት አሳስቦኛል አለ
አዲስ አበባ ነሓሴ 9/2010 በኢትዮጵያ በሴቶች ላይ የሚፈፀም በቡድን አስገድዶ የመድፈርና የአሲድ ጥቃት እንዳሳሰበው የኢትዮጵያ ህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ገለጸ። በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለመከላከል የህብረተሰቡን አመለካከት መለወጥ የሚያስችሉ ጠንካራ ተግባራት ሊከናወኑ እንደሚገባም ጠይቋል። የማህበሩ ሥራ አስፈጻሚ ዳሬክተር ወይዘሮ ሜሮን አራጋው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በቡድን አስገድዶ የመድፈርና በአካል ላይ አሲድ በመድፋት ሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን የተመለከቱ ተደጋጋሚ ቅሬታዎች ለማህበሩ እየቀረቡ ናቸው። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በ2007፣ በ2009 እና በ2010 ዓ.ም በሴቶች ላይ የአሲድ መድፋት ጥቃት መፈጸሙን የሚገልጽ ሪፖርት ለማህበሩ ቀርቧል። ከባህርዳር፣ ከአዲስ አበባ እና ከአዲግራት ከተሞች የተነገሩት እነዚህ ጥቃቶች የተፈፀሙት በትዳር እና በፍቅር ተጓዳኞች አማካኝነት መሆኑ ደግሞ ችግሩን አሳሳቢ እንደሚያደርገው ነው ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተሯ ያመለከቱት። "አሲድ ነው የምደፋብሽ" የሚለው ዛቻ አሁንም ድረስ በስፋት መኖሩን የሚያመላክቱ ጥቆማዎች ለማህበሩ እየደረሱት እንደሆነ የገለፁት ወይዘሮ ሜሮን "ይህም ሴቶች ላይ ለሚፈጸም ጥቃት አሲድ እንደ ጦር መሳሪያ እየተቆጠረ መምጣቱን ያሳያል" ብለዋል። በቡድን አስገድዶ የመድፈር 'አውሬነት' የተላበሰ ተግባርም አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በስፋት እየተስተዋለ ስለመሆኑም የማህበሩ ኃላፊ ተናግረዋል። አዲስ አበባ ጀሞ አካባቢ ከሁለት ወራት በፊት በአራት ወንዶች የተደፈረችን ሴት ለአብነት ያነሱት ወይዘሮ ሜሮን በአፋርና ሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎችም ተመሳሳይ ጥቃቶች እንደሚፈጸሙ ሪፖርት እንደሚደርሳቸው ገልጸዋል። በተለያዩ ማህበራዊ ጫናዎች እና የግንዛቤ ጉድለት ሳቢያ በርካታ ሳይነገሩ ተደብቀው የሚቀሩ የመድፈር ጥቃቶች ሊኖሩ አንደሚችሉም የሚገመት መሆኑን አመልክተዋል። "ይህም በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው መልካም እሴት እየተሸረሸረ፤ ሰብአዊነትም እየራቀ መምጣቱን ማሳያ ነው" የሚሉት የማህበሩ ሥራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር ጉዳዩ ትልክ ትኩረትን እንደሚሻም አሳስበዋል። የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር ችግሩ አሳሳቢ በመሆኑ ህጋዊ እርምጃዎችን ከመውሰድ ጎን ለጎን ችግሩን ለመከላከል የሚያስችል የግንዛቤ ማስፋት ስራ በዋነኛነት እያከናወነ እንደሚገኝ ተጠቁሟል። ሚኒስትሯ ወይዘሮ ያለም ጸጋዬ እንደተናገሩት በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ የኃይል ጥቃቶችን ለማስቆም መንግስት ከሚሰራው ተግባር በተጓዳኝ የህብረተሰቡን አመለካከት መቀየር ትልቁን ድርሻ ይይዛል። በመሆኑም ጉዳት ፈጻሚዎቹን ለፍርድ ከማቅረብ በተጨማሪ ግንዛቤ ለመፍጠር የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀትንና የመረጃ ስርጭትን ለማስፋት የተለያዩ መርሃ-ግብሮች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል። በዚህም በ2010 ዓ.ም ችግሩ ጎልቶ በሚታይባቸው አካባቢዎች ከተውጣጡ 500 የአገር ሽማግሌዎች፣ የፍትህ አካላት፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች ጋር በጉዳዩ አስከፊነት ላይ የመከረ መድረክ ተካሂዷል። የኢትዮጵያ ህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ባለፉት 6 ወራት ከወንጀል፣ ከሰራተኛና አሰሪ እንደዚሁም ከባልና ሚስት አለመግባባት ጋር በተያያዘ ካስተናገዳቸው 4 ሺህ ጉዳዮች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት የባልና ሚስት ናቸው።