ዲፕሎማቶች በአገር ገጽታ ግንባታ ላይ በመስራት በርካታ ቱሪስት ወደ ኢትዮጵያ መሳብ አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
ዲፕሎማቶች በአገር ገጽታ ግንባታ ላይ በመስራት በርካታ ቱሪስት ወደ ኢትዮጵያ መሳብ አለባቸው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 13/2014(ኢዜአ) ዲፕሎማቶች በአገር ገጽታ ግንባታ ላይ በመስራትና በማስተዋወቅ በርካታ ቱሪስት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ማድረግ አለባቸው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ አስታውቀዋል።
ላለፉት 10 ቀናት ስልጠና ላይ የቆዩ ዲፕሎማቶች በመዲናዋ የሚገኙ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል።
ዲፕሎማቶቹ በዛሬ ውሏቸው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ የከተማ ማስዋብ ስራ አካል የሆኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ነው የጎበኙት።
ከጉብኝታቸው በኋላ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየትም የፕሮጀክቶቹ ለአገልግሎት መብቃት ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና እያደረገች ላለችው ጉዞ ማሳያ ነው ብለዋል።
በተለይም የፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ መጠናቀቅ የተያዘው የእድገት ጉዞ በታሰበው መንገድ እየተመራ እንደሆነ እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
ከአሜሪካ ሎስ አንጀለስ የኢትዮጵያ ቆንጽላ ጽህፈት ቤት የመጡት አቶ ሙክታር መሀመድ እና ከኢንዶኔዥያ የኢትዮጵያ ኢምባሲ የመጡት የቀድሞ የጋምቤላ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋትልዋክ ቱት የመዲናዋ ገጽታ ማራኪ ሆኖ መቀየሩን ገልጸዋል።
በተመለከቱት ነገርም ደስ እንደተሰኙ ገልጸው፤ መንግስት ከፍተኛ የለውጥ ሃሳብ ያለው መሆኑን የሜጋ ፕሮጀክቶቹ ውጤት አመላካች ነው ብለዋል።
የከተማዋ የቀድሞ ገጽታ ያውቁት ከነበረው በእጅጉ መቀየሩን የገለጹት ደግሞ ከቤልጅየም ብራስልስ እና ከዋሽንግተን የኢትዮጵያ ኢምባሲዎች የመጡት አቶ ሙላት ባልቻ እና አቶ ስንታየሁ ሁንዴ ናቸው።
ኢትዮጵያ ቱሪስቶችን የሚስቡ በርካታ የተፈጥሮ ሃብቶቿን በጥቂቱ በማልማት የመስህብ ስፍራ በማድረግ ተጠቃሚ እንድትሆን ማድረግ ተገቢና ትክክለኛ ውሳኔም ነው ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ዲፕሎማቶች የአገር ገጽታ ግንባታ ላይ በመስራትና ገጽታውን በማስተዋወቅ በርካታ ቱሪስት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
ፕሮጀክቶቹ ከዲፕሎማቶቹ ተልዕኮ ጋር የሚያያዙ በመሆናቸው በአገር ገጽታ ግንባታና ማስተዋወቅ ላይ መስራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።