ቀጥታ፡

አሜሪካ 453 ሺህ 600 ብልቃጥ የኮቪድ-19 ክትባት ለኢትዮጵያ ሰጠች

አዲስ አበባ፤ መስከረም 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሜሪካ 453 ሺህ 600 ብልቃጥ የኮቪድ-19 ክትባት ለኢትዮጵያ ድጋፍ አደረገች፡፡

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓሲ ክትባቱን ለጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሰሃረላ አብዱላሂ አስረክበዋል።

የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ የበርካታ ሰዎች ሕይወት እያለፈ መሆኑን፣ ወደ ፅኑ ህክምና ክፍል የሚገቡ ታማሚዎች ቁጥርም ማሻቀቡን ተናግረዋል።

በዓለም ላይ በከፍተኛ ደረጃ የሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈ ያለው ዴልታ የተሰኘው የኮሮና ቫይረስ ዝርያ   በኢትዮጵያም በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ በመሆኑ የጥንቃቄ መንገዶች በተገቢው መንገድ እንዲተገበሩ አሳስበዋል።

ጤና ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር ባካሄደው ጥናት ቀደም ሲል ሕዝቡ 70 በመቶ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ይጠቀም እንደነበረ አስታውሰው ይህ ምጣኔ ወደ 20 በመቶ መውረዱን ተናግረዋል፡፡

ይህ መዘናጋት ቫይረሱ በከፍተኛ ደረጃ እንዲሰራጭ በር የሚከፍት በመሆኑ የጥንቃቄ መንገዶችን በተገቢው መንገድ መተግበር እንደሚገባ በአፅንኦት ተናግረዋል።

በትራንስፖርት አገልግሎት መስጫዎች ርቀትን አለመጠበቅ፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አለመጠቀም በስፋት ይስተዋላል ብለዋል።

አሜሪካ አራት ጊዜ ጆንሰን ጆንስን የተሰኘውን የኮቪድ ክትባት ድጋፍ ማድረጓን የገለፁት ወይዘሮ ሰሃረላ የዛሬው ድጋፍ ክትባቱን በስፋት ለመስጠት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ከቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ውስጥ ለሚገኙ ወገኞች ክትባት ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

አምባሳደር ጊታ ፓሲ በበኩላቸው መንግስታቸው ኢትዮጵያ የዜጎቿን ጤንነት ለመጠበቅ የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዛሬው ድጋፍ በተጨማሪ በቅርብ ቀናት 504 ሺህ ብልቃጥ ክትባት ድጋፍ እንደምታደርግም ገልፀዋል።

መንግስታቸው ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብልቃጥ በላይ ክትባት ለኢትዮጵያ ድጋፍ ማድረጓን የገለፁት አምባሳደሯ ይህም የአገራቱን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ጥንካሬ ያሳያል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ እስካሁን 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች የኮቪድ መከላከያ ክትባት መውሰዳቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

አገሪቷ ካላት የሕዝብ ቁጥር አንፃር ምጣኔው አነስተኛ በመሆኑ ተጓዳኝ ሕመም ያለባቸውና በዕድሜ የገፉ ሰዎች ወደ ጤና ጣቢያ በመሄድ ክትባት እንዲወስዱ እየተደረገም ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም