ቀጥታ፡

የህብረተሰቡ ተሳትፎ ለፖሊስ የጸጥታ ስራዎች ትልቅ አቅም እየፈጠረ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) የህብረተሰቡ ተሳትፎ ፖሊስ ለሚያከናውናቸው የወንጀል መከላከልና የጸጥታ ስራዎች ትልቅ አቅም እየፈጠረ መሆኑን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወንጀል መከላከል ዘርፍ ያሰለጠናቸውን ከ27 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞችን  አስመርቋል።

ስልጠናው በወንጀል መከላከል፣በህገወጥ ንግድ ቁጥጥር፣ በሰላም ግንባታ እና በበጎ ፈቃደኝነት ላይ እንደሆነ በምርቃት ስነ ስርአቱ ላይ ተመላክቷል።

"እኔ ለከተማዬ ሰላም ዘብ ነኝ" በሚል መሪ ሃሳብ በተሰጠው ስልጠና 27 ሺህ 540 ወጣቶች ለምረቃ መብቃታቸውም ተገልጿል

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር  ጌቱ አርጋው፤ ተመራቂዎች ለፖሊስ ስራ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ህብረተሰቡ ለጸጥታው ስራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸው፤ ህዝብን ያላሳተፈ የጸጥታ ስራ ምንም አይነት ውጤት እንደማይኖረው ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ ይህንን ለማጠናከር በሁሉም ክፍለ ከተማዎች እና ወረዳዎች የህዝብ አማካሪ ምክር ቤት በማቋቋም ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ማዕከል ሀላፊ አቶ መለስ አለሙ፤ ''ተመራቂዎች የኢትዮጵያ የመነሳት ዘመን ቀዳሚ ተሰላፊ በመሆናችሁ ልትኮሩ ይገባል'' ብለዋል።

ከዚህ በኋላም ለከተማው የጸጥታ መዋቅር አጋዥ በመሆን የአካባቢያቸውን ሰላም ለማስጠበቅም ብርቱ ስራ እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።

ወጣቶቹ የተሰጣቸውን ሀላፊነት በመገንዘብ በቅንነት እና በታማኝነት እንዲያገለግሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ተመራቂዎቹ በበኩላቸው የተሰጣቸውን ሀላፊነት በአግባቡ በመወጣት የአካባቢያቸውን ብሎም የከተማዋን ሰላም ለማረጋገጥ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

በቀጣይም በመዲናዋ የሚከበሩ የህዝብ በዓላት በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄዱ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም