ቀጥታ፡

የአፋር ህዝብ የህወሓትን ሀገር የማፍረስ እኩይ ዓላማ በማክሸፍ የሀገር ባለውለታነቱን በተግባር አሳይቷል

ሠመራ ፤መስከረም 13/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያዊነትን ዋጋና ትርጉም ጠንቅቆ የሚያውቀው የአፋር ህዝብ የህወሓትን ሀገር የማፍረስ እኩይ ዓላማ በማክሸፍ የኢትዮጵያ ባለውለታነቱን በተግባር አሳይቷል" ሲል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ገለጸ።

ፓርቲው አሸባሪው ህወሓት በአፋር ክልል በፈጸመው ወረራ  ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ700 ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ  የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሶች  ድጋፍ አድርጓል።

ዛሬ በአፋር ጭፍራ ወረዳ ተገኝተው ድጋፉን ያስረከቡት የፓርቲው ዋና ጸሐፊ አቶ አበበ አካሉ ፤የአሸባሪወ ህወሓት የሀገር ክህደት ወንጀል ዛሬ ድንገት የተፈጠረ ሳይሆን ለዘመናት ሲያቀነቅነው የቆየ መሆኑን አውስተዋል።

ኢትዮጵያ በዘመናት የትውልድ መስዋዕትነት ታፍራና ተከብራ የቆየች  መሆኗን አስታውሰው፤ "አሁን ሀገር ለማፍረስ የተነሳውን አሸባሪው ቡድን ለመመከት ልዩነትን በመተው ህብረትን ማጠንከር ይገባል" ብለዋል።

የኢትዮጵያዊነትን ዋጋና ትርጉም ጠንቅቆ የሚያውቀው የአፋር ህዝብ ሀገር የማፍረስ እኩይ ዓላማውን ለማሳካት በአፋር የወጪና ገቢ ንግድ መስመር ለመዝጋት የመጣውን አሸባሪው የህወሓት ዓላማ መክቶ ማክሸፉን ገልጸዋል።

"በዚህም የህወሓትን ህልም ቅዠት በማድረግ የሀገር ባለውለታነቱን በተግባር አሳይቷል" ብለዋል።

ለዚህ ጀግና ኩሩ ኢትዮጵያዊ ህዝብ ተጋድሎ በሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ሁሌም ሲታወስ እንደሚኖር ገልጸው፣ "ፓርቲውም ለህዝቡ የላቀ አክብሮት አለው" ሲሉም አስታወቀዋል።

 "አሸባሪው ህወሓት በንጹሀን ላይ ለፈጸመው ጅምላ ግድያ ፓርቲው ጥልቅ ሀዘን ተሰምቶታል፤ ድርጊቱንም አጥብቆ ያወግዛል " ብለዋል።

የሽብር ቡድኑን ለማስወገድ ፓርቲው አባላቱን በማስተባበር ከመንግስት ጎን እንደሚቆም ገልጸው፤ በዚህም ከዕለት ደራሽ እርዳታ ጀምሮ እስከ መልሶ ማቋቋም ግዴታውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።   

ዛሬ  ዋጋቸው ከ700 ሺህ ብር በላይ የሆኑ አልባሳት፣ ንጽህና መጠበቂያ ሳሙና፣ ስኳር ፣ፓስታና የተለያዩ አልሚ ምግቦችን ፓርቲው ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉን በአፋር ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የቅድመ ማስጠንቀቀና ፈጣን ምላሽ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አይዳሂስ ያሲን ተረክበዋል።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን በክልሉ በፈጸመው ወረራ የተፈናቀሉ ወገኖቻችን ለመደገፍ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ያደረጉት ተሳትፎ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ኢዜማ ያሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነታቸውን ትተው በሀገርና ዜጎች ጉዳይ ከመንግስት ጎን በጋራ በመቆም የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት ያደረጉት ተሳትፎ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።

ፓርቲው ላደረገው  ድጋፍ በተጎጂዎች ስም ምስጋና ያቀረቡት ዳይሬክተሩ፤ በቀጣይም ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም  ድጋፉ  ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።


በአፋር ክልል በአሸባሪው የህወሃት ቡድን  ለተፈናቀሉ ወገኖች ከተለያዩ አጋር አካላት ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የገንዘብና የዓይነት  ድጋፍ መሰብሰቡን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም