ቀጥታ፡

የኪነ-ጥበብና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የግድቡን ኃይል የማመንጨት ጅማሮ ዘካሪ ስራዎች እንዲሰሩ ጥሪ ቀረበ

መስከረም13/2014 (ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ሃይል ማመንጨት አስመልክቶ የኪነ-ጥበብና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች አይረሴ ስራዎች እንዲሰሩ የግድቡ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ጥሪ አቀረበ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከሁለት ወራት በኋላ በሁለት ተርባይኖች የመጀመሪያውን ዙር ሃይል የማመንጨት ስራ ይጀምራል።

"ጥምረት ለፍትህ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ትስስር" ዓላማን የሚያስተዋውቅ የውይይት መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

የ"ጥምረት ለፍትህ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ትስስር" ዓላማ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚደረገውን ሁለገብ ተሳትፎ ማሳደግና ዲጂታል ንቅናቄ መፍጠር መሆኑም ተገልጿል።

የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ የግድቡን ግንባታ አጠናቆ ሃይል ማመንጨት ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት መሰረት መጣል መሆኑን ተናግረዋል።

አንዳንድ አካላት ግብጽና ሱዳን የሚያራምዱትን የተሳሳተ አካሄድ ተቀብለው የኢትዮጵያን ልማት ለማስተጓጎል የሚያደርጉትን ያልተገባ ተጽዕኖ መታገል ከግድቡ ግንባታ ጎን ለጎን ሊሰራበት የሚገባ ተግባር መሆኑንም አንስተዋል።

ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ በግድቡ ላይ የያዘውን ኢ-ፍትሃዊ አቋም ማስቀየር ደግሞ ከኪነ-ጥበብና ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ባለፈ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ግዴታ ነው ብለዋል ዶክተር አረጋዊ።

ጽህፈት ቤቱ ባለበት ዘርፈ ብዙ ውስንነት በተለያዩ ቋንቋዎች ሕዝባዊ ንቅናቄ የማድረግ እጥረት እንደነበረበት ጠቅሰው በዓረብኛ፣ እንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎች መልዕክቶችን ለማስተላለፍ የፕሮዳክሽን ክፍል እንደሚያቋቁም ጠቁመዋል።

ግድቡ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት መሰረት ከመሆን ባሻገር "አይቻልም የተባለው ተችሎ የታየበት" የጽናትና የትብብር ምሳሌ መሆኑን በዲጂታል ሚዲያው ለዓለም ማሳወቅ ይገባል ነው ያሉት።

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍቅርተ ታምር በበኩላቸው በኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትብብር እየተገነባ ያለው የሕዳሴ ግድብ ፍሬ ሊያፈራ ጥቂት ቀርቶታል ሲሉ ተናግረዋል።

የኪነ-ጥበብና የማስታወቂያ ባለሙያዎች የግድቡን ሃይል የማመንጨት ሂደት አይረሴ በሆኑ ስራዎች ለሕዝቡ ማሳወቅና ግንዛቤ መፍጠር እንደሚጠበቅባቸውም አመልክተዋል፡፡

ግድቡ ከሁለት ወራት በኋላ የመጀመሪያ ዙር ሃይል እንደሚያመነጭ ገልጸው፤ ይህን ታሪካዊ አጋጣሚ በተለያዩ ስራዎች ለሕዝብ ተደራሽ ማድረግና ንቅናቄ መፍጠር እንደሚገባም ተናግረዋል።

የኪነ-ጥበብና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የሕዳሴ ግድቡን በማስተዋወቅና የሕዝቡን ተሳትፎ በማሳደግ በኩል ላበረከቱት አስተዋጽኦ አመስግነው በቀጣይም ተከታታይ ስራዎች በመስራት ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ግንዛቤ  እንዲፈጥሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ የኪነ-ጥበብ፣ የማስታወቂያና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የሕዳሴ ግድቡን ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ በማስተዋወቅና የአገር ውስጥ ንቅናቄ በመፍጠር እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብቷ የመጠቀም መብቷን ማንም ሊነጥቃት እንደማይችል ጠቅሰው በራስ አቅም የሚገነባውን የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከፍጻሜ ማድረስ የሁሉም ዜጋ ግዴታ ነው ብለዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አፈጻጸም 85 በመቶ ደርሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም