ቀጥታ፡

"ቻይና ለኢትዮጵያ የችግር ጊዜ ከጎኗ በመቆም አጋርነቷን ያሳየች ወዳጅ አገር ናት"

መስከረም13/2014 (ኢዜአ) ቻይና ለኢትዮጵያ በችግሯ ወቅት ከጎኗ በመቆም ጠንካራ ወዳጅነቷን በተግባር ያሳየች አገር ናት ሲሉ በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ አምባሳደር ደዋኖ ከድር ገለጹ።
የሁለቱን አገራት ግንኙነት ይበልጥ ማጎልበት የሚቻልባቸውን አቅሞች መጠቀም ይገባልም ብለዋል።

በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ አምባሳደር ደዋኖ ከድር ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነትና በመከባበር ላይ የተመሰረተ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የራሷን ችግሮች በራሷ የመፍታት አቅም እንዳላትና የውጭ ጫና አገሪቷ ላይ ማድረግ ተቀባይነት እንደሌለው ስትገልጽ መቆየቷን ተናግረዋል።

በዚህም ቻይና ኢትዮጵያ በችግር ውስጥ በምትገኝበት ጊዜ ከጎኗ በመቆም ጠንካራ ወዳጅነቷን አሳይታለች ብለዋል።

በርካታ የቻይና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እያፈሰሱ መሆኑንና የሁለቱ አገራት የኢኮኖሚ ግንኙነትም እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያና ቻይና ያላቸውን ጠንካራ ትብብር ይበልጥ የሚያሳድጉበት አቅም አለ ያሉት አምባሳደሩ አገራቱ በዚህ ዙሪያ ትኩረት ሰጥተው መስራት አለባቸው ብለዋል።

"ቻይና ትልቋ የኢትዮጵያ አጋር ናት፤ አሁንም ጠንካራ ወዳጅ ሆና ትቀጥላለች" ብለዋል አምባሳደር ደዋኖ።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዣኦ ሊጂያን ትናንት በሰጡት መግለጫ "ቻይና በሌሎች አገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ለመግባት በማዕቀብ አማካኝነት ጫና ለማሳደር ወይም ማዕቀብ ለመጣል የሚደረግን ማስፈራሪያ ትቃወማለች" ብለዋል። 

አሜሪካ በኢትዮጵያ ሠላምና መረጋጋት እንዲኖር ገንቢ ሚና መጫወት እንደሚጠበቅባትም አመልክተዋል።

"ቻይና የአገራት የእርስ በእርስ ግንኙነት በዓለም አቀፍ ግንኙነት መርህና በዓለም አቀፍ ሕግ መመራት እንዳለበት በጽኑ ታምናለች" ነው ያሉት።

"ኢትዮጵያ በአፍሪካ የቻይና ዋነኛ አጋር ናት፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ አካላት ልዩነቶቻቸውን ለመፍታት ፍላጎትና አቅም እንዳላቸው እናምናለን" ብለዋል።

ኢትዮጵያ በቅርቡ ብሔራዊ እርቀ ሠላም ላይ ትደርሳለች፤ ሠላምና ደህንነቷን ታረግጣለች ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ብለዋል ቃል አቀባዩ ዣኦ ሊጂያን።

ኢትዮጵያና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1970 ሲሆን በኢኮኖሚ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት ጠንካራ ትስስር አላቸው።

ቻይና በኢትዮጵያ በምታደርገው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በቀዳሚነት የምትጠቀስ አገር ናት።

በተጨማሪም ቻይና ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል በምታደርገው ጥረት ክትባትን ጨምሮ የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍም እያደረገች ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም