ዋናዋና የመንግስት አገልግሎቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የመስጠት ስራው በታሰበለት ፍጥነት እየተተገበረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዋናዋና የመንግስት አገልግሎቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የመስጠት ስራው በታሰበለት ፍጥነት እየተተገበረ ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 13/2014(ኢዜአ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር 170 አይነት የመንግስት አገልግሎቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመስጠት ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ ገለጸ።
የሚኒስቴሩ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር ኢንጂነር አብዮት ሲናሞ ለኢዜአ እንደገለጹት ዜጎች ዋና ዋና የመንግስት አገልግሎቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲያገኙ የማድረግ ስራው በታሰበለት ፍጥነት እየተተገበረ ነው።
በእስካሁን ሂደትም 34 ተቋማት በዲጂታል ቴክኖሎጂ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውንና በዚህም በአጠቃላይ 178 አገልግሎቶችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
አገልግሎቱን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የሚያገኘው ተጠቃሚ ቁጥርም ሁለት ሚሊዮን መድረሱን ገልፀዋል።
የአገልግሎቶቹን አይነት በዚህ ዓመት ወደ 400 ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ዶክተር ኢንጂነር አብዮት ተናግረዋል።
የዲጂታል ቴክኖሎጂ መስፋፋቱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑንና በተለይ ለወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር በር ከፋች እንደሆነም አክለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባካሄደው ጥናት በዓለም ላይ በዲጂታል ኢኮኖሚ የሚንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን ከሶስት ትሪሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን ጠቅሰው ወጣቱ የዚህ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
ዳይሬክተር ጄኔራሉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ወጣቶች ይህን ምቹ ሁኔታ መጠቀም እንዲችሉ ስልጠና እየሰጠ መሆኑንም ገልጸዋል።
አገልግሎቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ መስጠት በኢትዮጵያ ባለመለመዱ በርካታ የሰው ሃይል፣ ጊዜና ገንዘብ ሲባክን መቆየቱን በስልጠናው የተሳተፉ ወጣቶች ገልጸዋል።
የዲጂታል ቴክኖሎጂ አገልግሎት እየተስፋፋ መምጣቱም ይባክን የነበረውን ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ ከመቆጠብ ባሻገር ሙስናና የቢሮክራሲ ችግሮችን እንደሚፈታም ተናግረዋል።
ወጣት ቃልኪዳን ተስፋዬ የተገልጋይ ጊዜና ጉልበት ብክነት መቀነስ የሚያስችል አሰራር መሆኑ ትገልፃለች።
ወጣት ሩሃማ ጌታነህ በበኩሏ የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ባጭር ጊዜና ያለ ምንም መሰልቸትና ችግር ሳይኖር ብዙ ወጪ ሳናወጣ አገልግሎት የምናገኝበት ነው ትላለች፡፡
አሰራሩ ቢለመድ ደግሞ የበለጠ ትልቅ ደረጃ መድረስ እንችላለን ብዬ አስባለሁ ነው ያለችው።
አገልግሎት አሰጣጡ ወደ ኤሌክትሮኒክስ ሲቀየር ድካምና ወጪ ይቀንሳል የሚል እምነት እንዳለው አንስቶ ሊደገፍና ሊበረታታ የሚገባው አሰራር ነው ያለው ወጣት አቤኔዘር አስራት ነው፡፡
ከንግድ ፈቃድ ማውጣት፣ ማደስ፣ ጡረታና ተያያዥ ጉዳዮች፤ የአየር መንገድ ትኬት መቁረጥ፣ ለአገር አቋራጭ ተሽከርካሪ ድንበር ለማቋረጥ ፈቃድ መስጠትና ወዘተ በዲጂታል ቴክኖሎጂ አገልግሎት መስጠት ከጀመሩት 178 አገልግሎቶች መካከል ይጠቀሳሉ።