ቀጥታ፡

አሜሪካም ሆነ ምዕራባዊያን የኢትዮጵያን የህዝቦቿን ደህንነት የመጠበቅ መብት ሊያከብሩ ይገባል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 13/2014 አሜሪካም ሆነ ምዕራባዊያን የኢትዮጵያን የህዝቦቿን ደህንነት የመጠበቅ መብት ሊያከብሩ ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ገለጹ።

የኢትዮጵያ መንግስት እየተወጣ ያለው ህዝቡን ከአሸባሪው የህወሃት ሃይል ነጻ የማውጣት ግዴታው መሆኑን አብራርተዋል።

ኃያላን አገራት ከአሸባሪው ህወሓት ጎን መቆማቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን እንደሚያሻክረው ገልጸዋል።

መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበርና የአገር ህልውናን ለመጠበቅ በአሸባሪው ህወሓት ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ የሚቃወሙ አገራት ኢትዮጵያ ጠንክራ እንዳትወጣ የሚፈልጉ ናቸው ሲሉም ጠቁመዋል።

አሸባሪው ህወሓት በኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጽመውን ግፍ እያዩ እንዳላዩ በማለፍ መንግስት የህግ ማስከበር እርምጃ ሲወስድ የሚጮሁት የኢትዮጵያን ዕድገት ስለማይፈልጉ መሆኑን ነው አጽንኦት የሰጡት።

ፕሮፌሰር በየነ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኃያላኑ አገሮች የአሸባሪውን ጥፋት ደግፈው መቆማቸው በጣም የሚያሳፍር ነው።

"አሸባሪው ህወሓት የሰው ልጅ በአምሳያው ላይ ያደርሳል የማይባል ወንጀል መፈጸሙን እያወቁና እየተመለከቱ በዝምታ መደገፋቸው ተቀባይነት የለውም" ብለዋል።

መንግስታቱ በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና ማድረስ የሚፈልጉት የግል ዓላማቸውን ለማስፈጸም በማሰብ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ የአሸባሪውን ህወሓት እኩይ ሴራ ለማጋለጥና የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም  ለማሳወቅ በንቃት መስራት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።

አሜሪካና ምዕራባውያኑ አገሮች ኢትዮጵያን በተመለከተ የሚከተሉት አካሄድ ፍርደ ገምድልና የተሳሳተ መሆኑንም አብራርተዋል።

የአሜሪካ መንግስት በራሱ ግዛት ውስጥ አንዱ ክልል የህግ ጥሰት ቢፈጽም በቸልታ እንደማያልፈው ጠቁመው፤ "በእኛ ላይ ሲሆን መቃወሙ ተቀባይነት የለውም" ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት አሸባሪው ቡድን በህዝብና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያስከትል እርምጃ መውሰዱ ከአንድ መንግስት የሚጠበቅ ትክክለኛ እርምጃ መሆኑንም ገልጸዋል።

መንግስት የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ቀዳሚ ኃላፊነቱ መሆኑን ጠቁመው፤ "ሌሎች አገራት በአገራችን የውስጥ ጉዳይ ለመግባት የሚያደርጉት ሙከራ ተቀባይነት የለውም" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ከውጭ የሚሰማውን ጩኽት ወደ ጎን በመተው "በአንድነት ለአገሩ በመቆም፣ ለሰራዊቱ ድጋፍ በማድረግ መተባበር አለበት" ብለዋል፡፡

ወጣቱም ሰራዊቱን ለመቀላቀል እያሳየ ያለውን ተነሳሽነት አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

የተለያዩ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የአሸባሪው ቡድን ተከፋይና ምንዳ ለቃሚዎች በመሆናቸው ነባራዊውን እውነታ አዛብተው እያቀረቡ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም