ቀጥታ፡

የባይደን አስተዳደር ኢትዮጵያን ላይ የሚያደርገው ዕጅ ጥምዘዛ ተቀባይነት የለውም

አዲስ አበባ መስከረም 13/2014 (ኢዜአ) የባይደን አስተዳደር ኢትዮጵያ ላይ የሚያደርገው ዕጅ የመጠምዘዝ ሙከራ ተቀባይነት የለውም ሲሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።
የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች "የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት" ዘመቻን ተቀላቅለዋል።

ዘመቻውን ዛሬ የተቀላቀሉት አዲስ ትውልድ ፓርቲ፣ ሕዳሴ ፓርቲ፣ ራያ ራዩማ ፓርቲና የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር ናቸው።

ኢትዮጵያ በየዘመናቱ በምዕራባዊያን ክህደትና ጫና ሲፈጸምባት እንደነበር ያወሱት የፓርቲዎቹ ተወካዮች፣ ለአሸባሪው ህወሓት በመወገን ኢትዮጵያን እጅ ለመጠምዘዝ መሞከር ተቀባይነት እንደሌለው ገልጸዋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን የመንግስትን የተኩስ ማቆም ውሳኔ እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ በአማራና በአፋር ክልሎች የፈጸመውን የንጹሃን ጭፍጨፋ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ተቋማትን የማውደም ግፎች የምዕራባዊያን ሚዲያዎች እንዳላዩ አልፈውታል ብለዋል።

አሸባሪ ቡድኑ ከሸኔና ከጉሙዝ ታጣቂዎች ጋር ተጣምሮ አገር ለማፍረስ እየሰራ መሆኑን ገልፀው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች አገር ለማፈራረስ የተነሱ የባዕዳን አገራት ተላላኪዎችን እንደሚያወግዙ አስታውቀዋል።

የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ዋና ጸሃፊ አቶ ክፍለማርያም ሙሉጌታ ምዕራባዊያንና ተላላኪዎቻቸው ኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ጫና እየበረታ መምጣቱን አንስተዋል።

አሸባሪው ህወሓት የ1977ቱን ድርቅ ተከትሎ ለእርዳታ የመጣ እህል በመሸጥ የጦር መሳሪያ ሲገዛ እንደነበር በማስታወስ፤ ዛሬም በምዕራባዊያን እርዳታ ተመሳሳይ ድርጊት እየፈጸመ ስለመሆኑ አንስተዋል።

ምዕራባዊያን ከሽብር ቡድኑ ጋር ያላቸው ቁርኝትም ተልዕኳቸውን የሚያስፈፅም ተላላኪና ኢትዮጵያን ጠል ሃይል በመሆኑ ነው ብለዋል።

የአገር ሕልውና አደጋ ውስጥ ሲገባ ሁሉንም የሚመለከት በመሆኑ ፓርቲያቸው አገር የማዳን ዘመቻውን መቀላቀሉን ገልጸዋል።

የራያ ራዩማ ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ኅላፊ አቶ ጌታቸው ከበደም ቡድኑ ለ27 ዓመታት የዘረጋውን የውጭ ግንኙነት በመጠቀም በዘረፈው ሀብት ሎቢስቶች ቀጥሮ የኢትዮጵያ ገጽታ የማጠልሸት ሴራ እያካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ፓርቲያቸው ዘመቻውን የተቀላለው የኢትዮጵያ ሕልውናና ጥንካሬ እንዳይቀጥል የሚደረገውን ኢ-ፍትሃዊና የተሳሳተ አካሄድ በመቃወም ነው ብለዋል።

"የአገር ሕልውና ማስቀጠል የሁላችንም የጋራ ግዴታ ነው" ያሉት አቶ ጌታቸው፤ የባይደን አስተዳደር የኢትዮጵያን እጅ የመጠምዘዝ ጥረት ተቀባይነት እንደሌለው ተናግረዋል።

የምዕራባዊያን ጫና ለዘመናት ኢትዮጵያ ላይ የበረታ እንደነበረ ያስታወሱት የሕዳሴ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ አቶ ሱራፌል እሸቱ ደግሞ ብርቱውን ጫና አባቶች በጋራ ክንድ መክተው ሉዓላዊነቷን አስጠብቀው ቆይተዋል ይላሉ።

አሁንም በተለይ አሸባሪው ቡድን በፈጠረው ጦርነት የምዕራባዊያን ተጽዕኖ እየበረታ መምጣቱን ገልጸው፤ ኢትዮጵያን ጫና ውስጥ ለመክተት የእርዳታ ኢ-ፍትሃዊነትም ተስተውሏል ብለዋል።

"ይህን መመከት የምንችለው በጋራ ክንዳችን ነው" ያሉት አቶ ሱራፌል፤ በአገራችን ጉዳይ በጋራ ከቆምን "ኢትዮጵያ ለማንም አትንበረከክም" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም