ቀጥታ፡

የመሬት መራቆትን ለመከላከል ሰፊ የምርምርና የልማት ስራ ሊከናወኑ እንደሚገባ ተገለፀ

አዳማ ነሀሴ 9/2010 በሀገሪቱ ደረቅና ከፊል ደረቃማ በሆኑ አካባቢዎች እየተስፋፋ የመጣውን የመሬት መራቆትና በረሐማነት ለመከላከል ሰፊ የምርምርና የልማት ስራዎች ሊካሄዱ እንደሚገባ የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር አስታወቀ ። በደረቅና ከፊል ደረቃማ አካባቢዎች ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት አያያዝን ተግባራዊ ማድረግ በሚቻልበት ዙሪያ የሚመክር አገር አቀፍ አውደ ጥናት  በአዳማ ከተማ ተካሄዷል። በመድረኩ ላይ የተገኙት የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ይማም እንዳስታወቁት በሀገሪቱ በመሬት አጠቃቀምና አያያዝ ጉድለት የተነሳ የአፈር፣ የደን፣ የውኃ፣ የእንስሳትና የሌሎችም ዕፅዋት ሀብት ለጉዳት ተዳርጓል። መንግስት ይህንን ችግር በመገንዘብ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማትና የተራቆቱ ቦታዎችን ከልሎ እንዲያገግሙ በተጠናከረ ሁኔታ በመስራቱ በርካታ ውጤት ተመዝግቧል፡፡ ነገር ግን በደረቅና ከፊል ደረቅ በሆኑ አካባቢዎች ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት አያያዝን ተግባራዊ ለማድረግና በረሐማነትንና የመሬት መጎሳቆልን ለመከላከል ጥረት ቢደረግም የሚፈለገው ለውጥ እንዳልተገኘ ገልፀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአካባቢዎቹ እየታየ ያለው የደን ዕፅዋትና የተፈጥሮ ሃብት መመናመን በምርታማነትና በህብረተሰቡ አኗኗር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያስከተለ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አስታውቀዋል። በመሆኑም በደረቅና ከፊል ደረቅ በሆኑ አካባቢዎች የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለባቸው ያለውን ተፅእኖ ለመከላከል ሰፊ የምርምር፣ የልማትና የግንዛቤ ማሳደግ ስራ በቀጣይ መከናወን እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል፡፡ በኢትዮጵያ የአካባቢ እና የደን ምርምር ኢንስቲትዩት የሰው ሰራሽና ጥምር እርሻ ደን ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ተሾመ ተሰማ በበኩላቸው በአገሪቱ የሚገኝ 22 ሚሊዮን ሄክታር የተራቆተ መሬት መልሶ እንዲያገግም እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ለዚህ ስኬት ኢንስቲትዩቱ ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር በርካታ የምርምር ስራዎች እያካሄደ ሲሆን በተለይ ጠቃሚና ተስማሚ የዛፍ ዝርያዎችና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች ምን ላይ ማተኮር እንዳለባቸው የመለየት ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የዓውደ ጥናቱ ዋና ዓላማም በተለይ የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከልና ኑሮ ከማሻሻል አንፃር እስካሁን የተከናወኑ የምርምር ሥራዎች ያስገኟቸው ውጤቶች ባለድርሻ አካላት እንዲታወቁ ማድረግ መሆኑን ጠቅሰዋል። እንደ ዶክተር ተሾመ ገለፃ በረሐማነትንና የመሬት መጎሳቆልን ለመከላከል በሚንቀሳቀሱ አካላት መካከል በቀጣይ ሊኖር ስለሚገባው ትብብር በአውደ ጥናቱ ውይይት ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያ የአካባቢ እና የደን ምርምር ኢንስቲትዩት ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው በዚሁ አውደ ጥናት ላይ ከከፍተኛ ትምህርትና ምርምር ተቋማት የተካሄዱ ከ15 የሚበልጡ የምርምር ስራዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ የቀረቡትን የምርምር መረጃዎችንና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በደረቅና ከፊል ደረቅ በሆኑ አካባቢዎች ዘላቂ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ለማረጋገጥ እንዲሁም በረሐማነትንና የመሬት መጎሳቆልን ለመከላከል የሚያስችል አቅም ይፈጠራል ተብሎ ይጠበቃል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም