አሸባሪው ሕወሓት በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በፈጸማቸው ኢ - ሰብዓዊ ድርጊቶች የአሸባሪነቱን ጥግ አሳይቷል - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ሕወሓት በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በፈጸማቸው ኢ - ሰብዓዊ ድርጊቶች የአሸባሪነቱን ጥግ አሳይቷል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 13/2014(ኢዜአ) አሸባሪው ሕወሓት በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በፈጸማቸው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች የአሸባሪነቱን ጥግ በተጨባጭ ያሳየ መሆኑን መመልከታቸውን በተለያዩ ግንባሮች ጉብኝት ያደረጉ የመገናኛ ብዙሃን አመራር አባላት ገለጹ።
የመገናኛ ብዙሃን ኃላፊዎቹ በአሓዱ ሬዲዮ በሚዘጋጀው 'ከአሓዱ መድረክ' ፕሮግራም ላይ ቀርበው ያዩትን ነገር አብራርተዋል።
ቡድኑ በሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ጎንደርና ሰሜን ጎንደር አካባቢዎች አሸባሪው ያደረሰውን ጉዳትና ውድመትም ተዘዋወሮ መመልከቱ ተገልጿል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ አሸባሪው ዘግናኝ ጭፍጨፋ መፈጸሙን መመልከታቸውን ተናግረዋል።
የቡድኑ ዓላማ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ማፍረስ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ቢቂላ፤ ክስተቱ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እጅግ ዘግናኝና እጅግ በጣም አሳዛኝ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል እንደሆነም ገልጸዋል።
ቡድኑ በተመለከታቸው አካባቢዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ "በዘር ጭፍጭፋ ሊጠቀስ የሚችለና በጦር ወንጀልም ሊያስጠይቅ የሚችል ነው" ይላሉ።
በዚህ ሂደት ውስጥ ምንም የማያውቁ ህጻናት፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች በዚህ ቡድን መጨፍጨፋቸውን እንደተመለከቱ አንስተዋል።
ጥፋቱ በሰብዓዊ ቀውስ ላይ ብቻ ያነጣጠረ ሳይሆን የአካባቢው ንጹሃን ዜጎች የሚጠቀሙባቸውን ንብረቶች ዘረፋ ውድመት ተፈጽሟል።
በዚህም ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ የህዝብ አስተዳደር ተቋማትና ሌሎች ቁሳዊ ውድመቶች መድረሱን ማየታቸውን ነው የተናገሩት።
ኢትዮጵያ በዚህ ዓይነት ቡድን መተዳደሯ እጅግ የሚያሳዝን አጋጣሚ ሆኖ እንዳገኙትም ዶክተር ቢቂላ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው፤ የቡድኑ አሻባሪነት ልክ 'ወደር የሌለው' መሆኑን እንደታዘቡ ገልጸዋል።
''ቡድኑ ምንም ዓይነት የሰብዓዊነት ርህራሄ የሌለው፣ የሰውና የህዝብ ባህሪ ያልተላበሰ ሁነኛ አሸባሪ መሆኑን አስመስክሯል'' ነው ያሉት።
ቡድኑ ባያቸው አካባቢዎች ከአንድ ቤተሰብ በርካታ ንጹሃንን አረመኔያዊ ተግባር እንደፈጸመ ማየታቸውን ነው የጠቆሙት።
"ቡድኑ ያደረሰውን ጉዳት ሚዲያ ብቻ ሳይሆን ሰዓሊያን፣ ቀረጺያንና ሌሎችም አካላት ማየት አለባቸው" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ ናቸው።
ምክንያቱም መገናኛ ብዙሃን እያሳዩ ያሉት ከተፈጸመው እጅግ ውስን የሆነውን ነው በማለት ያብራራሉ አቶ ጌትነት።
ለዚህ የተለያየ ምክንያት ማቅረብ ቢቻልም ይህ ክስተት በየትኛውም የዓለም ክፍል እንዳይደገም በሚያስተምር መልኩ መረጃው መጠናቀር እንዳለበትም አመልክተዋል።
የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሓመድ ኢድሪስም እንዲሁ ወደ ስፍራው ከመሄዳቸው በፊት በሚዲያ የሚያውቁት ቢሆንም፤ ቦታው ላይ ሲደርሱ ግን አስደንጋጭ ነገር ማየታቸውን ገልጸዋል።
አሸባሪ ቡድኑ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በሙሉ ሕዝብንና ታሪክን ለማጥፋት አልሞ መምጣቱን መገመት አይከብድም ባይ ናቸው።
"በተፈጸመው ድርጊት አሸባሪ ቡድኑ በአካባቢው ላይ 'የማይሽር ጠባሳና የማይድን ቁስል' ጥሎ ነው የሄደው" ብለዋል አቶ መሓመድ።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ አሸባሪ ቡድኑ ካደረሰው ጉዳትና ውድመት አኳያ መገናኛ ብዙሃን በተገቢው መንገድ ለህዝቡ እንዳላሳወቁ መረዳት መቻላቸውንም እንዲሁ።
ሁሉም የመገናኛ ብዙሃን አመራር አባላት በአካባቢው ከደረሰው ከፍተኛ ጉዳት አኳያ ዜጎቹን ለማቋቋም ትልቅ ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ነው ያመለከቱት።