የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን አዲስ የጉምሩክ አሰራር ሥርዓት ተግባራዊ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን አዲስ የጉምሩክ አሰራር ሥርዓት ተግባራዊ አደረገ
አዲስ አበባ ነሓሴ 9/2010 የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በዘመናዊ የመረጃ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የጉምሩክ አሰራር ሥርዓት በ11 ጣቢያዎች ተግባራዊ ማድረጉን አስታወቀ። ባለስልጣኑ ቀድሞ ይገለገልበት የነበረውን አሰራር በአዲስ መቀየሩን አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። አዲሱ "የጉምሩክ ሥራ አመራር ስርዓት" ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የጉምሩክ አሰራር ሥርዓት ጋር ተመሳሳይ አገልግሎት መስጠት እንድትችል የሚያግዝ ነው። በባለስልጣኑ የጉምሩክ ሥራ አመራር ሥርዓት ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ አባቡ እምሩ እንዳሉት፤ ባለስልጣኑ ቀድሞ ይጠቀምበት የነበረው አሲኩዳ (ASYCUDA++) የተባለው የጉምሩክ አሰራር ሥርዓት እየተሻሻለ ከመጣው የጉምሩክ አሰራር ጋር አብሮ አይሄድም። በመሆኑም ከዓለም ዓቀፍ የጉምሩክ አሰራር ጋር አብሮ የሚሄድ በዘመናዊ የመረጃ ቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አስረድተዋል። በዘመናዊ የመረጃ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የጉምሩክ አሰራር ሥርዓት ቀልጣፋ፣ ዘመናዊና ግልጽነት የሰፈነበት አሰራር ለመዘርጋት ታስቦ እንደሆነም ገልጸዋል። አዲሱ የጉምሩክ አሰራር ሥርዓት እ አ አ 2017 ጀምሮ በጋላፊ፣ በሚሌና በቃሊቲ የጉምሩክ ጣቢያዎች የሙከራ ሥራ እንደ ጀመረ ያስታወሱት ሥራ አስኪያጁ በአሁኑ ወቅት ከ80 እስከ 85 በመቶ በደረቅ ወደቦች ተግባራዊ መደረጉን ተናግረዋል። በባለስልጣኑ የጂቡቲ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤትን ጨምሮ የአዳማ፣ የሞጆ፣ የምሥራቅ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የገላን፣ የቃሊቲ እና የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ የገቡ የጉምሩክ ጣቢያዎች መሆናቸውን አስረድተዋል። ሥርዓቱ እስከ ታህሳስ ወር 2011 ዓ.ም ድረስ በሁሉም ጣቢያዎች ተግባራዊ እንደሚደረግ የገለጹት አቶ አባቡ በትግበራ ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮች ማስተካከያ እየተደረገባቸው እንደሚሄድ ጠቁመዋል። ባለስልጣኑ በወጪና ገቢ ንግድ ላይ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ስልጠና የሰጠ ሲሆን ከትራንስፖርት ባለስልጣን እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል። አዲሱ የጉምሩክ አሰራር የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ወጪ እና ገቢ የሚያደርጉት ዕቃ የት እንደደረሰ ምን ያህል ክፍያ መፈጸም እንደሚጠበቅባቸው የኢንተርኔት አገልግሎት ባለበት ቦታ ሆነው መከታተል የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል። እንዲሁም ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመቀነስ፣ የንግድ ሥርዓቱን ለማቀላጠፍ፣ የደንበኞችን እርካታ ለማሳደግና ግልጽነት ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል።