ሰባት ቡና አልሚዎችና አቅራቢዎች ማኅበር ለመመስረት ስምምነት ፈረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ሰባት ቡና አልሚዎችና አቅራቢዎች ማኅበር ለመመስረት ስምምነት ፈረሙ
አዲስ አበባ መስከረም 13/2014(ኢዜአ) በቡና ማልማት፣ ማዘጋጀትና ማቅረብ ስራ የተሰማሩ ሰባት ማኅበራት 'የኢትዮጵያ ቡና ማኅበር'ን ለመመስረት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮጵያ ቡና አልሚዎች፣ የሲዳማ ቡና አቅራቢዎች፣ የኦሮሚያ ቡና አዘጋጅና አቅራቢዎች፣ የደቡብ ቡና አቅራቢዎች፣ የኢትዮጵያ ቡና አልሚዎች፣ የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎችና የሴቶች ቡና ማኅበራት ናቸው።
የሚመሰረተው ማኅበር ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ፣ የኢትዮጵያን ቡና በዓለም ገበያ ከፍተኛ ተቀባይነት እንዲኖረው የማድረግ፣ አርሶ አደሩን በጋራ የመደገፍና በምርቱ ልክ ተጠቃሚ የማድረግ ዓላማ ያለው ነው።
በተጨማሪም ህገወጥ ግብይት በማስቀረት በጋራ መስራት እንደሚያስችል ተገልጿል።
በፊርማ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ዑመር የማኅበራቱ ወደ አንድ ማኅበር መሰባሰብ የሚኖረውን ጠቀሜታ አስረድተዋል።
ማኅበሩ ለአርሶ አደሩ ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ በአገሪቷ ብዛትና ጥራት ያለው ቡና በማምረት ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬን ለማግኘት የተሻለ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ሶስት ዓመታት በነበረው ለውጥ የገበያ አማራጮችን በማስፋት አገሪቷን በቡና ምርት ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለና በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 907 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልፀዋል።
በ2014 በጀት ዓመት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማግኘት መታቀዱን የገለፁት አቶ ሻፊ ባለፈው ነሀሴ ብቻ 32 ቶን ቡና ወደ ውጭ ተልኮ 123 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ደሳለኝ ጀና እውቀትና አቅማችንን በማሰባሰብ በአንድ ማኅበር መሰባሰባችን የቡና ምርትና ምርታማነትን የበለጠ ለማሳደግ ይረዳናል ብለዋል፡፡
ማኅበሩ ከመንግስት ጎን ሆኖ ጥናትና ምርምር በማካሄድ በዘርፉ የተሻለ የአሰራር ስርዓት እንዲዘረጋ ግብዓት እንደሚያዘጋጅም ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት ሀብታችንን በጋራ እንዳይለማ ተደርገን ቆይተናል ያሉት የኦሮሚያ ቡና አዘጋጅና አቅራቢዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ፈጠነ የኋላእሸትም ለውጡ የአገራችንን ሀብት አልምተን እኩል ተጠቃሚ እንድንሆን ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮልናል ብለዋል።
በቀጣይ በአንድ ጠንካራ ማኅበር ተካተን አገራችንን እናለማለን ሲሉም አክለዋል።