ቀጥታ፡

በማዕከላዊ ሰሜን ሪጅን የአራተኛው ትውልድ ፈጣን የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት ተጀመረ

ደብረ ብርሃን ፤ መስከረም 13/2014(ኢዜአ) ኢትዮ-ቴሌኮም በማዕከላዊ ሰሜን ሪጅን አራተኛው ትውልድ /4ጂ/ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ ፈጣን የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

አገልግሎቱ የደብረ ብርሃን፣ ፍቼ፣ ሸዋ ሮቢት፣ ሱሉልታ፣ ሸኖ፣ ሰንደፋ፣ ገብረ ጉራቻና ለገጣፎ ከተሞች የሚገኙ የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን በማስጀመሪያ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።

የኢትዮ- ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ እንዳሉት፤ ካምፓኒው ከፍተኛ የዳታ አጠቃቀም በሚታይባቸው የሃገሪቱ ከተሞች የአራተኛውን ትውልድ ፈጣን የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት ለማስፋፋት እየሰራ ይገኛል።

ባለፉት ጊዜያት በሌሎች አካባቢዎች አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው፤ ዛሬ በማዕከላዊ ሰሜን ሪጅን የሚገኙ ከተሞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ አገልግሎት መጀመሩን አስታውቀዋል።

የአራተኛው ትውልድ /4ጂ/ ኢንተርኔት የላቀ ፍጥነትና አስተማማኝ ዳታ የሚሰጥ በመሆኑ ደንበኞች አገልግሎቶቻቸውን በማቀላጠፍ ምርታማነታቸውን ለመጨመር እንደሚያስችላቸው ዋና ሰራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል።

ኢትዮ-ቴሌኮም እስካሁን ባደረጋቻው የአራተኛ ትውልድ ማስፋፊያ ስራዎች የዛሬውን ጨምሮ በአዲስ አበባና ሌሎችም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ 86 ከተሞችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለም ገልጸዋል።

የካምፓኒው አገልግሎት መስፋፋትም በመረጃ የበለፀገ ማህበረሰብና ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የጎላ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል።

በቀጣይም የአምስተኛው ትውልድ አገልግሎት ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑም ተመልክቷል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም