በ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወዳድረው ላሸነፉ የፓርላማ አባላት ስልጠና እየተሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወዳድረው ላሸነፉ የፓርላማ አባላት ስልጠና እየተሰጠ ነው
አዲስ አበባ መስከረም 13/2014 (ኢዜአ) በ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወዳድረው ላሸነፉ የፓርላማ አባላት ስልጠና እየተሰጠ ነው።
ስልጠናው በዋናነት የሕዝብ ተወካዮች ሚና፣ የአባላት ስነ ምግባር ደንብ እና በምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
የስልጠናው ዓላማ የምክር ቤቱ አባላት ስራዎቻቸውን ያለምንም የመረጃ እጥረት እንዲያከናውኑ ማገዝ እንደሆነም ተጠቁሟል።
ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በተካሄደው አገራዊ ምርጫ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ሕዝቡ የሌሊት ቁርና ዝናብ ሳይበግረው በነቂስ በመውጣት ድምጹን ለመረጠው ፓርቲ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው ውጤትም የብልጽግና ፓርቲ መንግስት መመስረት የሚያስችለውን አብላጫ ድምጽ አግኝቷል።
የምርጫውን ዴሞክራሲያዊነት እና ተዓማኒነት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጭምር የመሰከሩለት ሲሆን ውጤቱን በፀጋ መቀበላቸውንና ከአሸናፊው ፓርቲ ጋር ለመስራት መዘጋጀታቸውን ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው።