ቀጥታ፡

በአሸባሪው ህወሃት ተፈናቅለው ለከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ለተዳረጉ ዜጎች ድጋፍ እናደርጋለን

መስከረም 13/2014 (ኢዜአ) በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህፃናት አድን ድርጅት ( 'ዩኒሴፍ)' በአሸባሪው የህወሃት ወራሪ ኃይል ተፈናቅለው በሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ።

የድርጅቱ የአገር ውስጥና የዋና መስሪያ ቤት የስራ ኃላፊዎች በአሸባሪው የህወሃት ወራሪ ኃይል ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በደሴ ከተማ የተጠለሉ ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱም በኢትዮጵያ የዪኒሴፍ ተወካይ አዴል ኮደር፣ የብሪታኒያ ልዩ መልዕክተኛ ኒክ ዳየር፣ ከዩኒሴፍ ዋናው መስሪያ ቤት የአቅርቦት ክፍል ኃላፊ ኢትሌቫ ካድሊል፣ በዩኒሴፍ የባህርዳር ፊልድ ኦፊሰር ባልደረቦችና ሌሎች አካላት ተገኝተዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አበበ ገብረ-መስቀል፤ አሸባሪው ህወሃት በአማራና በአፋር ክልሎች ወረራ ከፈጸመበት ሰዓት አንስቶ በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትና ዝርፊያ እየፈጸመ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በሽብር ቡድኑ ወረራ ሳቢያም በአማራ ህዝብ ላይ ከፍተኛ መፈናቀል በመከሰቱ በደሴ ከተማና አካባቢዋ በ15 መጠለያ ጣቢያዎች ከ300 ሺህ በላይ ዜጎች በከፍተኛ ሰብዓዊና ማህበረዊ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በመንግስት፣ በተራድኦ ድርጅቶችና ግለሰቦች አማካኝነት የሚቀርበውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ድጋፍ ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ከተፈናቃዩ ቁጥር መብዛት አኳያ ሰፊ ክፍተት መኖሩን ተናግረዋል።

በተለይም ወራሪው የሽብርተኛ ኃይል በተቆጣጠራቸው የሰሜን ወሎና አካባቢው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በምግብ እና በህክምና እጦት በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ሁሉም ግብረሰናይ ድርጅቶችና ሁሉም ኢትዮጵያዊ የችግሩን ስፋት በሚገባ በመረዳት ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ የዪኒሴፍ ተወካይ አዴል ኮደር፤ በአሸባሪው ሕወሃት አማካኝነት ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ህፃናት፣ እናቶች እና አቅመ ደካሞች እስከ ሶስት ቀን ድረስ በእግር በመጓዝ እዚህ መድረሳቸውን መስማት ስሜቱ ከባድ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ እንደገለጹት፤ በግጭት ምክንያት ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉትን ለማገዝ የተያዩ የድጋፍ ስራዎች ተከናውነዋል።

በሰሜን ጎንደር ደባርቅ ለሚገኙ የህክምና ማዕከላት የሚሆኑ የህክምና ቁሳቁሶችንና ለአዲስ ተፈናቃይ የሚውሉ ኃይል ሰጭ ምግቦችን ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።

"በአማራ ክልል በርካታ ስራዎችን አከናውነናል። እኔም በአካባቢው ያለውን ሁኔታ ለመረዳት ከአንድ ወር በፊት የደባርቅ ጉብኝት አካሂጃለሁ።

በስፍራውም ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች መኖራቸውን ምልከታ በማድረግ በሰሜን ጎንደር ለህክምና ማዕከላት የሚውሉ የተወሰኑ የህክምና ቁሳቁሶችን፣ አዲስ ተፈናቃይ ለሆኑ ዜጎች የሚውሉ ኃይል ሰጪ ብስኩቶችን ድጋፍ አድርገናል።" በማለት ገልጸዋል።

ከዚህ በፊትም እስከ 2 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር የሚያወጡ ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጋቸውን በማስታወስ፤ በቀጣይም ሃብት በማሰባሰብ አፋጣኝ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ለማገዝ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም