አሸባሪው ህወሓት በአማራ ክልል 19ሺህ የሚጠጉ የንግድ ቤቶችን ዘርፏል - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሓት በአማራ ክልል 19ሺህ የሚጠጉ የንግድ ቤቶችን ዘርፏል
ባህር ዳር፤ መስከረም 12/2014(ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት ወረራ በፈጸመባቸው የአማራ ክልል አምስት ዞኖች 19ሺህ የሚጠጉ የንግድ ቤቶችን ሙሉ በሙሉ መዝረፉን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ አስታወቁ።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት፤ ቡድኑ በደረሰባቸው አካባቢዎች የፈጸመው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሰብአዊ ቀውስ ወረራውን ሆን ብሎ ስለመካሄዱ ማሳያ ነው።
"የታቀደና የተጠና ወረራ መሆኑም ቡድኑ ወረራ በፈጸመባቸው በአምስት ዞኖች የተካሄደው የመጀመሪያ ዳሰሳ ጥናት አመላካች ነው" ብለዋል።
እንደ ዶክተር ፋንታ ገለጻ፤ አሸባሪው ህወሓት በወረራቸው የሰሜን ወሎ፣ ዋግ ኽምራ ፣ ሰሜን ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር እና የደቡብ ወሎ ዞኖች 19ሺህ የሚጠጉ የንግድ ቤቶችን ሙሉ በሙሉ ዘርፏል።
"ቁጥሩ ሆቴሎችንና የግል መኖሪያ ቤቶችን አይጨምርም" ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው በብድር የሚሰሩ ወጣቶች ሱቆች ሳይቀር በቡድኑ መዘረፉንም አመላክተዋል።
ይህም ወጣቶቹ ሰርተው ለመለወጥ ያደርጉት የነበረውን ጥረት ያሰናከለ እኩይ ድርጊት መሆኑን አመልክተዋል።
ወረራው በክረምት ወቅት መፈጸሙ አርሶ አደሩ መሬቱን በዘር እንዳይሸፍንና ቀድሞ የተሸፈነውም እንዲወድም አድርጓል።
ይህም ክልሉ በዘላቂነት በችግር ውስጥ እንዲኖር ለማድረግ አሸባሪው ህወሓት ከበፊትም ጀምሮ ያለውን እሳቤ እንደሚያሳይ ነው ዶክተር ፋንታ ያስረዱት።
"ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶችም ሆኑ ሌሎች ድጋፍ የሚያድርጉ አካላት አሸባሪው በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ከ4 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በአስከፊ ሁኔታ ግፍና በደል እየተፈጸመባቸው መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል" ብለዋል።
ከዚህ ውስጥ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ህዝብ ምንም ዓይነት ጥሪት የሌለውና በምግብ ዋስትና የሚደገፍ እንደነበር ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አውስተዋል።
ለእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች አፋጣኝ የምግብ፣ የጤናና ሌሎች ድጋፎች እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።
በሽብር ቡድኑ ምክንያት ከማምረት ውጭ የሆነው ህዝብ እንስሳቱ የታረዱበትና የተገደሉበት በመሆኑ ከእለት ምግብ ድጋፍ ባሻገር ዘላቂ የማቋቋም ሥራ እንደሚጠይቅም አመላክተዋል።
"አሸባሪው ቡድን ተሸንፎ በለቀቃቸው አካባቢዎች የግለሰብ ንብረት፣ የመንግስት ተቋማት ሃብት፣ የማህበራዊ አገልግሎት መስጫዎችና መሰረተ ልማቶች ከአገልግሎት ውጭ መሆናቸው ተረጋግጧል" ብለዋል ዶክተር ማንደፍሮ።
የጥፋት ቡድኑ በማይካድራ የፈጸመውን የጅምላ ጭፍጨፋ በቆቦ፣ በሰሜን ጎንደር ጭና እና ሌሎች አካባቢዎች መድገሙን መረጃዎች እያመላከቱ ነው።
ይህን መሰረታዊ ሁኔታ በመረዳት ተጎጂዎች ወደቀደመ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ማህበራትና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲረባረቡም ጥሪ አቅርበዋል።
በተባበሩት መንግስታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) የኢትዮጵያ ተወካይ ፋጡማ ሰይድ በበኩላቸው፤ ድርጅታቸው በዘላቂ የእድገት ልማት ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በዚህም ተፈናቃዮችና በችግር ውስጥ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን በአነስተኛ መስኖ፣ በበልግና ሌሎች የእርሻ ወቅቶች በማሳተፍ የምርጥ ዘር፣ የማዳበሪያና ሌሎች ግብአቶችን እንደሚደግፉ ተናግረዋል።
"ይህም ወረራ በተፈጸመባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ፈጥነው እንዲቋቋሙና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የነበራቸውን ሚና እንዲጫወቱ ያደርጋል" ብለዋል።
የተፈናቀሉና የንግድ ድርጅቶቻቸው የተዘረፉባቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማቋቋም ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር ተባብረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
መንግስት የተነጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአማራ እና አፋር ክልሎች ወረራ በመፈጽም ከፍተኛ የሆነ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት ማድረሱ ይታወቃል።