ቀጥታ፡

አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ከነክፉ ሃሳቡ ገድለን እንቀብረዋለን

ደሴ መስከረም 12/2014 (ኢዜአ) ''በየደረሰበት በንጹሀን ላይ ግፍና ሰቆቃ እየፈጸመ ያለውን አሸባሪ ቡድን ከነክፉ ሃሳቡ ገድሎ ለመቅበር እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ቆርጠን ተነስተናል'' ሲሉ መከላከያን የተቀላቀሉ ወጣቶች ተናገሩ።

በደቡብ ወሎ ዞን መከላከያን ለመቀላቀል የተመዘገቡ ወጣቶች ዛሬ በደሴ ከተማ የሽኝት መርሀግብር ተደርጎላቸዋል።

በእዚህ ወቅት የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪ ወጣት አማረ በላይ በሰጠው አስተያየት አሸባሪው ህወሓት ዕድሜ ልኩን በአገርና በህዝብ ላይ የፈፀመው ግፍ አልበቃው ብሎ አሁንም አገር ለማፍረስ መፍጨርጨሩ  ቁጭት እንደፈጠረበት ተናግሯል።

ይህን ዓላማውን ለማሳካት አማራና አፋር ክልሎችን በመውረር በንጹሀን ዜጎች ላይ ግፍና ሰቆቃ መፈጸሙ እረፍት እንደነሳው ጠቁሞ፣ "የጥፋት ቡድኑ እንዲደመሰስ እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ቆርጫለሁ" ብሏል።

''ለዚህም በስልጠና በመታገዝ አሸባሪውን ህወሓት ፊት ለፊት ለመፋለም መከላከያን ተቀላቅያለሁ" ያለው ወጣቱ፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ሰላም በዘላቂነት ለማስጠበቅ የሚጠበቅበትን ለመወጣት ዝግጁነቱን አረጋግጧል።

"አሸባሪው የህወሓት ቡድን በሴቶች፣ ህጻናትና አረጋዊያን ላይ ሳይቀር እየፈጸመ ያለውን ዘግናኝ ግፍ ለመበቀል ህይወቴንም ጭምር አሳልፌ እሰጣለሁ" ያለችው ደግሞ ሌላዋ የመቅደላ ወረዳ ነዋሪ ወጣት አማከል ተስፋዬ ናት፡፡

"በየቀኑ የምንሰማው የእህት ወንድሞቻችን ልቅሶና የምናየው እምባ እንዲቆም መከላከያ ሰራዊቱን ተቀላቅያለሁ" ያለቸው ወጣቷ፣ ቡድኑ ዳግም ስጋት እንዳይሆን በቆፈረው ጉድጓድ ለመቅበር እንደምትሰራ ገልጻለች።

"ሁላችንም የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ከፍለን ህዝብና አገራችን ከወራሪው ኃይል ነጻ ማውጣት አለብን" ብላለች።

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በዘላቂነት ማስጠበቅም ለመንግስት ብቻ የሚተው እንዳልሆነም ነው የገለጸችው።  

አባቷም ወታደር መሆኑን ጠቁማ፣ የሀገር ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ መከላከያን በመቀላቀሏ ደስተ መሆኗን ተናግራለች፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰይድ መሃመድ በበኩላቸው አሸባሪው ህወሓት አማራን አዳክሞ ኢትጵያን ለማፍረስ የወጠነውን ሴራ በቅንጅት ማክሸፍ የግድ የሚልበት ወቅት መሆኑን ገልጸዋል።

"አገር በጠላት ተወራ በህዝብ ለይ ግፍና ሰቆቃ ሲፈፀም ቁጭ ብሎ መመልከት ያልፈለጉና የአባቶቻቸውን ጀግንነት ለመድገም የቆረጡ ወጣቶች መከላከያን ተቀላቅለዋል" ብለዋል።

ወጣቶቹ በተደራጀ አግባብ የጥፋት ቡድኑን ለመደምሰስ ብቻ ሳይሆን በቀጣይ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ጉልህ ሚና እንዳላቸውም ተናግረዋል።

"በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ሕይወታቸውን ለአገርና ለህዝባቸው አሳልፈው ለመስጠት ቁርጠኛ የሆኑ ወጣቶች የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች መሆናቸውን በተግባር አስመስክረዋል" ብለዋል፡፡

በወጣቶቹ የሽኝት መርሃ ግበር ላይ የዞንና የወረዳ አመራሮች፣ የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም