ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ለአገር መከላከያ ሠራዊት 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

መስከረም 12/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ለአገር መከላከያ ሠራዊት 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም በየሁለት ወሩ በሚያሳትመው "ነጋሪ" መፅሄት ዋና ትኩረቱን በሕልውና ዘመቻ ላይ ያደረገ "ሺህ ዓመት ተፈትና ያሸነፈች አገር - ኢትዮጵያ" በሚል ያዘጋጀውን ልዩ እትም አንድ ሺህ ቅጂ ለመከላከያ ሠራዊት በስጦታ አበርክቷል።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ታደሰ ሀይለማሪያም ድርጅታቸው ለመከላከያ ሠራዊት ያደረገውን ድጋፍ ለመከላከያ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ ብርጋዴር ጄኔራል አስረስ አያሌው አስረክበዋል።

ድርጅቱ ለጀግናው የአገር መከላከያ ሠራዊት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልፀዋል።

ዋና ስራ አስፈፃሚ የድርጅቱ የስራ ሃላፊዎችና ሠራተኞች ቀደም ሲልም በግንባር እየተዋደቀ ለሚገኘው ሠራዊት ደም መለገሳቸውን አስታወሰዋል።

የገንዘብ ድጋፉ ከድርጅቱ ሠራተኞች የወር ደመወዝ የተዋጣ መሆኑንም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም "ሺህ ዓመት ተፈትና ያሸነፈች አገር - ኢትዮጵያ" በሚል በነጋሪ መጽሄቱ 18ኛ ልዩ እትም ያዘጋጀውን አንድ ሺህ ቅጂ ለአገር መከላከያ ሠራዊት በስጦታ አበርክቷል።

በኢዜአ የነጋሪ መጽሄት ምክትል ዋና አዘጋጅ አቶ ፍፁምእሸት ሽመልስ የመጽሄት ስጦታውን ለመከላከያ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ ብርጋዴር ጄኔራል አስረስ አያሌው አስረክበዋል።

ኢዜአ አሸባሪው ህወሓት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ሌሊት በአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝን በማጥቃት የአገር ክህደት ወንጀል በፈፀመበት ወቅት ለታሪክ ማጣቀሻ መሆን የሚችል ሰነድ ማዘጋጀቱን ገልፀዋል።

በዚህም አብይ ትኩረቱን በመከላከያ ሠራዊት የጀግንነት ተጋድሎ ላይ ያደረገ በኢዜአ ነጋሪ መጽሄት ልዩ እትም አንድ ሺህ ቅጂ ከዚህ ቀደምም ለመከላከያ ሠራዊት በስጦታ ማስረከቡን አስታወሰዋል።

ኢዜአ ዛሬም "ሺህ ዓመት ተፈትና ያሸነፈች አገር - ኢትዮጵያ" በሚል የተዘጋጀው ነጋሪ መጽሄት ልዩ እትም አንድ ሺህ ቅጂ ለአገር መከላከያ ሠራዊት በስጦታ ማበርከቱን ተናግረዋል።

የመከላከያ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ ብርጋዴር ጄኔራል አስረስ አያሌው አሸባሪው ህወሓት ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች መሰረተ ልማት በማውደም፣ ሕዝብ በማፈናቀል፣ ዘረፋና የሠብዓዊ መብት ጥሰት በመፈፀም የዘር ማጥፋትና የጦር ወንጀል እየፈፀመ ነው ብለዋል።

ይህ አሸባሪ ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ጥረት እያደረገ ቢሆንም በኢትዮጵያዊያን አንድነትና ትብብር ጥረቱ እንደሚከሽፍ በየግንባሩ እያጋጠመው ያለው ሽንፈት እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያን የማዳን ዘመቻው በጅምር ላይ ያለና ያልተጠናቀቀ በመሆኑ ሠራዊቱን በሰው ሀይል፣ በገንዘብ፣ በስንቅና በሞራል መደገፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅትና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላደረጉት ድጋፍና ስጦታም ምስጋና ችረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም