ቀጥታ፡

የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግስት ዘመቻ በኢትዮጵያ ላይ ኢ-ፍትሃዊ አመለካከት ላላቸው ምላሽ ይሰጣል

መስከረም 12/2014 (ኢዜአ)"የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግስት" ዘመቻ በሀሰት ፕሮፖጋንዳ ላይ ተመስረተው በኢትዮጵያ ላይ ኢ-ፍትሃዊ አመለካከት ላላቸው አገራት ምላሽ የሚሰጥ ነው ሲሉ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ካሳሁን ጎፌ ተናገሩ።

የሚኒስቴሩ ሠራተኞችና የአስር ተጠሪ ተቋማቱ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት "የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግስት" ዘመቻ መርሃ ግብር ተጀምሯል።

ዘመቻው ከነገ ጀምሮ በሚኒስቴሩ ሁሉም ተጠሪ ተቋማት እንደሚካሄድና ከ18 ሺህ በላይ ሠራተኞች እንደሚሳተፉበትም ተገልጿል።

ሚኒስትር ዴኤታው ካሳሁን ጎፌ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት አሸባሪው ቡድን አገር የማፍረስ ዓላማ አንግቦ በፈፀመው ወረራና ጥቃት ኢትዮጵያ ተገዳ ወደ ጦርነት መግባቷን አንስተዋል።

ይህ የቡድኑ አስጸያፊ ተግባር መላው ሕዝብ ለመከላከያ ሠራዊቱ ተጋድሎ በተለያየ መንገድ አጋርነቱን እንዲገልጽና ደጀንነቱን እንዲያሳይ ማድረጉንም ተናግረዋል።

አሸባሪው ቡድን ለፈጸመው የአገር ክህደት ወንጀል ከህልውና ዘመቻ የተሻለ አማራጭ እንደሌለ የተገነዘበው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጣውን ማሳየቱም በአገር ጉዳይ አንድ እንደሆነ ያሳየበት መሆኑን ተናግረዋል።

"የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግስት" ዘመቻም እንዲሁ በሐሰት ፕሮፓጋንዳ ላይ ተመስርተው በኢትዮጵያ ላይ ኢ-ፍትሃዊ አመለካከት ለያዙ አገራት ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም እንደ አሜሪካ ላሉ አገር ሳይሆን አንድ ቡድን ለሚያደምጡና ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር ለሚሞክሩ አገራት እውነታውን ለማስረዳት ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን ለመከላከያ ሠራዊቱ በተግባር እያሳዩት ያለውን ድጋፍና አጋርነት በ"የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግስት" ላይም በመሳተፍ ታሪክ እንዲያኖሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም