ቀጥታ፡

የሀገርን ሉዓላዊት ለማስከበር እየተካሄደ ባለው ትግል በመሳተፍ አስፈላጊውን መስዋዕትነት እንከፍላለን

ጎባ/ነገሌ ፤ መስከረም 12/2014 (ኢዜአ) የአሸባሪዎችን የጥፋት ተግባር በማክሸፍ የሀገርን ሉዓላዊት ለማስከበር እየተካሄደ ባለው ትግል በመሳተፍ አስፈላጊውን መስዋዕትነት እንደሚክፍሉ የባሌና ጉጂ ዞኖች ወጣቶች አስታወቁ፡፡

ከሁለቱ ዞኖች የተውጣጡ በርካታ ወጣቶች መከላከያን ለመቀላቀል ወደ ማሰልጠኛ ማዕከላት ሲንቀሳቀሱ አሸኛኘት ተደርጎላቸዋል።

ከባሌ ዞን አሸኛኘት ከተደረገላቸው ወጣቶች መካከል ከጎሮ ወረዳ የመጡት ወንድማማቾች እንዳለ ባጫና ገላዬ ባጫ ይገኙበታል።

በነፃነትና ሰላም መኖር የሚቻለው የሀገር ሉአላዊነት ሲከበር ብቻ መሆኑን በመገንዘብ በፈቃዳቸው የሀገር መከላከያ ስራዊት ለመቀላቀል መወሰናቸውን ነው ወንድማማቾቹ ለኢዜአ የተናገሩት።

ሀገርን ለማዳን የሚደረገው የህልውና ዘመቻ በስኬት እንዲጠናቀቅ  ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን በመሰለፍ የአሸባሪዎቹን የጥፋት ተግባር ለማክሸፍ አስፈላጊውን መስዋእትነት እንደሚከፍሉ አስታውቀዋል፡፡

ወጣት ሀሰን ከድር በበኩሉ "የሀገር ሉዓላዊነት ምልክትና ዓርማ የሆነው የመከላከያ ሰራዊት በፈቃደኝነት ለመቀላቀል እድሉን በማግኘቴ ከፍተኛ ሀገራዊ ኩራት ይሰማኛል" ብሏል፡፡

ከባሌ ዞን 12 ወረዳዎች የተውጣጡ ወጣቶች ለስልጠና በተሸኙበት ወቅት የተገኙት የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም አልይ፤ የህልውና ዘመቻው እንዲሳካ የዞኑ ማህበረሰብ እያደረገ የሚገኘው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"በተለይም የነገ ሀገር ተረካቢ ወጣቶች ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት አንድ ሆነው በመነሳት ኢትዮጵያን ከሽብርተኞች ጥቃት ለመጠበቅ ያሳዩት ቁርጠኝነት ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅርና ክብር ያሳያል" ነው ያሉት።

በባሌ ዞን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለህልውና ዘመቻው ድጋፍ የሚውል ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ማበርከታቸውንም ዋና አስተዳዳሪው አውስተዋል፡፡ 

በተመሳሳይ ከጉጂ ዞን  ወረዳዎችና ከተሞች የተውጣጡ ወጣቶች ወደ  ማሰልጠኛ ማዕከል  ተሸኝተዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ለመቀላቀል ለስልጠና ከተጓዙት መካከል የነገሌ ከተማ ነዋሪ  ወጣት ዘላለም መንግስቴ ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት "በህልውና ዘመቻው ሀገር  ለማዳን  መከላከያ ሰራዊቱን በመሰለፍ አስፈላጊውን መስዋእትነት እንደሚከፍል ተናግሯል፡፡

አሸባሪውን ህወሓት ለመደምሰስ በሚካሄደው ዘመቻ ለመሳተፍ በፈቃደኝነት መወሰኑን  ገልጿል።

ወጣት ጌትነት አስጨናቂ በበኩሉ "ተምሮ ስራ መያዝ፣  አግብቶና ልጅ ወልዶ  ለማሳደግ  በመጀመሪያ የሀገር ህልውና መከበር አለበት" ብሏል።

አባቶቻችን ደማቸውን አፍሰስውና አጥንታቸውን ከስክሰው የገነቧትን ሀገር አፈርሳለሁ ብሎ የተነሳን አሸባሪ ቡድን ለመደምሰስ እየተካሄደ ባለው ትግል ለመሳተፍ መነሳቱን አስታውቋል፡፡

የጉጂ ዞን ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ብዙነህ  ቦደና ባደረጉት ንግግር፤  ውትድርና  የሀገር  ህልውና ከማስከበር ጎን ለጎን በእውቀትና በሙያ የሚያበለጽግና የሚያስከብር  ሙያ ነው ብለዋል፡፡

የዞኑ ህዝብ ልጆቹን መርቆ በመላክ ጭምር በሁለንተናዊ ድጋፍና  ትብብር የኋላ  ደጀን  በመሆን ሀገር ለማዳን እያደረገ ላለው ጥረት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በሁለቱም ዞኖች ለዘማች ወጣቶቹ በተደረገው የአሸኛኘት ስነ-ስርዓት ላይ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የተገኙ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ርክክብ መካሄዱንም የኢዜአ ሪፖርተሮች ከጎባና ነገሌ ዘግበዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም