ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሃት ህዝቡን ከመበደሉም ባለፈ የክልሉን የተፈጥሮ ህብት ያለከልካይ በዝብዟል

አሶሳ  መስከረም 12/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት በህዝቦች ላይ ካደረሰው በደል በተጨማሪ የክልሉን የተፈጥሮ ሃብት ያለከልካይ በዝብዟል ሲሉ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኢዜአ ያነጋገራቸው የአሶሳ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ።

ነዋሪዎቹ የኢትዮጵያ አስተማማኝ ሠላም እስኪረጋገጥ ድረስ ለአገር መከላከያ ሠራዊት የምናደርገውን ድጋፍ እናጠናክራለን ብለዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል ወይዘሮ ሃሰኒያ ሱሊማን እንዳሉት በህወሓት የሽብር ቡድን አገር የማፍረስ ሴራ የአሶሳ ዞን ህዝብም ጉዳት ደርሶበታል፡፡

በተለይም ሴቶች እና ህጻናት የሽብር ቡድኑ ጥቃት ዋነኛ ሰለባ እየሆኑ ነው የሚሉት አሰተያየት ሰጭዋ “ሴቶች ከመከላከያ ጎን በመሆን የሽብር ቡድኑን መዋጋት ግዴታችን ነው” ብለዋል፡፡

የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለአገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ መስጠታቸውን የተናገሩት ወይዘሮ ሃሰኒያ እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈልም መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህዝቦች ላይ ካደረሰው በደል በተጨማሪ የክልሉን የተፈጥሮ ህብት ያለ ከልካይ በዝብዟል የሚሉት ደግሞ አቶ እንድሪስ አልመሃዲ የተባሉ የአሶሳ ዞን ነዋሪ ናቸው፡፡

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የክልሉ ህዝብ የህሓሃትን አገር የማፍረስ እኩይ ሴራ በሚገባ መረዳቱን አስታውሰዋል።፡

ከህወሓት ከማዕከላዊ መንግስት መወገድ በኋላ በገራዊ ጉዳዮች ላይ ድምጻቸው ከሌሎች ኢትዮጵያውን እኩል እየተሰማ መሆኑን ተናግረው የህወሃት የሽበር ቡድን አገር የማፍረስ ሴራ የማይሳካ እና መሠረተ ቢስ እንደሆነም አቶ እንድሪስ ጠቁመዋል፡፡

ለአገር መከላከያ ሠራዊት የምናደረገውን ድጋፍ በማጠናከር ለኢትዮጵያ አንድነት እስከ ህይወት መስዋዕትነት እንከፍላለን ብለዋል።

ወይዘሮ ሁዳ ከድር በበኩላቸው “የሽብር ቡድኑ በአማራ፣አፋርና በትግራይ ህዝብ በተለይም በሴቶችና ህጻነት ላይ የሚያደርሰው ጥቃት የእኛም ጥቃትና ጉዳት ነው” ብለዋል።

በክልሉ መተከል፣ካማሽና አሶሳ ዞኖች ላይ የሽብር ቡድኑ ተላላኪዎች የሚያደርሱት ጥቃት አሁንም ድረስ አለመቆሙን ጠቁመዋል፡፡

''ጥቃቱ ቁጭት በመፍጠር በኢትዮጵያዊ ስሜት ተነሳስተን የአገር መከላከያ ሰራዊትን እንድንደግፍ አድርጎናል'' ያሉት ነዋሪዋ ሴቶች በየአካባቢቸው ለሠራዊቱ የሚያዘጋጁትን ስንቅ በአብነት ጠቅሰዋል።

አገራችንን በምንም አይነት ለጠላት አሳልፈን አንሰጥም የሚሉት ወይዘሮዋ “የሽብር ቡድኑን አገር የማፍረስ ሴራ ለማክሸፍ እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን” ብለዋል፡፡

የአሶሳ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ እንድሪያስ መሐመድ ህወሓት እንደገለጹት ጥቅምት 24/2013 በአገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን እዝ አባላት ላይ በፈጸመው አስከፊ ጥቃት ከሁሉም ስፍራ የተወጣጡና የሁሉም የሆኑ የሰራዊቱ አባላት ተጎጂ ነበሩ፡

“ይህም የዞኑ ህዝብ የሽበር ቡድኑን እውነተኛ ማንነትና አገር የማፍረስ ድብቅ ሴራ ለማወቅ አስችሎታል” ብለዋል፡፡

በህልውና ዘመቻውም በሁለት ዙሮች በርካታ የክልሉ ተወላጆች የሃገር መከላከያ ሰራዊትን ለመቀላቀል ወደ ማሰልጠኛዎች የገቡ መሆናቸውን ገልጸው አስተዳደሩም የህልውና ዘመቻውን ከማገዝ ባለፈ ዞኑ ከሱዳን ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች ጸጥታን ማስጠበቅ ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በቅርቡ በተደረገው ሁለተኛ ዙር የአገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ ከዞኑ ህዝብ ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ በገንዘብና በአይነት መሰባሰቡን ከዞኑ አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም