ቀጥታ፡

በግብርና፣ ምግብና መጠጥ ማቀነባበርና የፕላስቲክ ህትመት የንግድ ትርኢት የ10 አገራት ኩባንያዎች ይሳተፋሉ

አዲስ አበባ መስከረም 12/2014 (ኢዜአ) በግብርና፣ ምግብና መጠጥ ማቀነባበርና የፕላስቲክ ህትመት የንግድ ትርኢት የ10 የተለያዩ አገራት ኩባንያዎች ይሳተፋሉ።

አራተኛው የኢትዮጵያ የግብርና፣ ምግብና መጠጥ ማቀነባበርና የፕላስቲክ ህትመት የንግድ ትርኢት ከጥቅምት 4 እስከ 6 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

የንግድ ትርኢቱ አዘጋጅ የሆኑት ፌር ትሬድ እና የፕራና ኤቨንት አዘጋጆች ከተለያዩ ተሳታፊ አገራት እምባሲ ተወካዮች ጋር በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል። 

የፕራና ኤቨንት ማኔጅንግ ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ለማ፤ መንግስት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በከፍተኛ ወጪ መገንባቱን አንስተዋል።

በመሆኑም የንግድ ትርኢትና ባዛር በኢንዱስትሪ ፓርክ የሚሰሩ ባለሃብቶች ዓለም የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ደረጃ እና ተሞክሮ ለመቅሰምና አላማቸውን ለማሳደግ ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በንግድ ትርኢቱ በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ ኩባንያዎች እንዲሁም የተለያዩ የውጭ አገራት ኩባንያዎች የሚካፈሉ መሆኑን ተናግረዋል።

ከቱርክ፣ ጀርመን፣ ጣሊያ፣ ፈረንሳይ፣ ህንድን ጨምሮ የ10 አገራት 40 ኩባንያዎችና ድርጅቶች ይሳተፋሉ ብለዋል።

የፌር ትሬድ መስራች ማርቲን ማሬዝ፤ የንግድ ትርኢቱ የእውቀትና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ጠቃሚ መሆኑን አብራርተዋል።

በዚህም የሀገር ውስጥ አምራቾች የእውቀት ሽግግር ለመፍጠርና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለማምረት እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።

በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክና ኢንዱስትሪ ልማት ማስተባበሪያ ዳይሬክተር አቶ አያልነህ አባዋ ኢትዮጵያ ለኢንዱስትሪ ልማት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህ ተግባርም መሰል የንግድ ትርኢቶች የኢንዱሪትር ሴክንተሩ በፍጥነት ለማሳደግ የላቀ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም