የቡድን 20 ሀገራት የብድር ኮሚቴ ያቀረበው የብድር ማገገሚያ የውሳኔ ሃሳብ ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
የቡድን 20 ሀገራት የብድር ኮሚቴ ያቀረበው የብድር ማገገሚያ የውሳኔ ሃሳብ ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ያደርጋል
መስከረም 12/2014 (ኢዜአ) የቡድን 20 ሀገራት የብድር ኮሚቴ ያቀረበው የብድር ማገገሚያ የውሳኔ ሃሳብ ኢትዮጵያን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ዛሬ በሰጠው መግለጫ የቡድን 20 ሀገራት የብድር ኮሚቴ በመስከረም 16 ቀን 2021 ባካሄደው ስብሰባ የብድር ማገገሚያ ስትራቴጂን ለማሻሻል ያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቋል።
ሚኒስትር ድኤታው ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ተሳታፊ በነበረችበት የኮሚቴው ውይይት ኢትዮጵያ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ምክረ-ሃሳቦች ቀርበዋል።
የኮሚቴው የብድር ማገገሚያ የውሳኔ ሃሳብ ለኢኮኖሚ ፍላጎቶች ተስማሚ የሆነ ብድር ለማቅረብ እና የታዳጊ ሀገራትን ማክሮ- ኢኮኖሚ ለማረጋጋት ጠቃሚ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።
የውሳኔ ሃሳቡ የአበዳሪ አገራትን የብድር አፈጻጸም የጋራ ማዕቀፍ መሰረት ያደረገና ኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚዋን ለማረጋጋት የምታደርገውን መሰረታዊ እርምጃ እንደሚደግፍም ነው ያነሱት።
በዚህም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የፈጠረውን የኢኮኖሚ ተጽእኖ ለመቋቋም ሚናው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኮሚቴው የጋራ ሰብሳቢዎች የሆኑት ፈረንሳይና ቻይና የአበዳሪዎች ኮሚቴ እንዲቋቋም ላደረጉት አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል።
የውይይት መድረኩ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አሁን ያለበት ሁኔታ ላይ ግንዛቤ መፍጠርን ጨምሮ ኢትዮጵያን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሃሳቦች የተነሱበት እንደነበርም አውስተዋል።
ኮሚቴው በቀጣይ ስብሰባው በኢትዮጵያ ያለው የእዳ ጫና ላይ ትንተና በማቅረብ ምን ያህሉ በእዳ ማገገሚያ ማእቀፍ ውስጥ ይካተት በሚለው ጉዳይ ላይ ምክክር ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም አንስተዋል።
ሚኒስቴሩ አሁን ላይ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ እና የተረጋጋ ኢኮኖሚ ለመፍጠር እየሰራ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
ከተለያዩ አበዳሪ አካላት ቃል የተገባ ብድር ለመሰብሰብ ከታቀደው 80 በመቶ በላይ እንዲሁም አዳዲስ ብድሮች በመፈራረም ረገድ ደግሞ ከ90 በመቶ በላይ አፈፃፀም መመዝገቡንም ነው የተናገሩት።
የአበዳሪ ሀገራት የጋራ ማዕቀፍ የቡድን 20 ሀገራትን እና የፓሪስ ክለብ የሚባሉትን አበዳሪዎች በማስተባበር የታዳጊ አገሮችን ዕዳ እንደየአገሩ ሁኔታ ለማጤን የሚያስችል ስርዓት እንደሚከተል ይታወቃል።
በሌላ ዜና የገንዘብ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት እንዲሁም የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሰራተኞች "የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት" ዘመቻን በይፋ ተቀላቅለዋል።