ቀጥታ፡

አሜሪካ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የምታደርገው ጣልቃ ገብነት ተቀባይነት የለውም

ሚዛን አማን፣ አርባምንጭ፤ መስከረም 12/2014 (ኢዜአ) አሜሪካ ዓለም አቀፍ ህጎችን በመጻረር በኢትዮጵ የውስጥ ጉዳይ ላይ የምታደርገው ጣልቃ ገብነት ተቀባይነት እንደሌለው ምሁራን አስታወቁ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሚዛን ቴፒና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን፤ አሜሪካ ዓለም አቀፉ ህግን በመጻረር በተለያዩ ሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ችግር እየፈጠረች መሆኑን ነው የተናገሩት።

ሀገራት ተስማምተው በፈረሙት ዓለም አቀፉ ህግ  አንድ ሀገር በሌላ ሀገር የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባት እንደማይችል መደንገጉን የጠቀሱት ምሁራኑ፤ ያዘዙትን የሚፈጽምና በራሱ የማይቆም ደካማ መንግስት በመመስረት የበላይነትን ማምጣት እንደማይቻል ገልጸዋል።

በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ የአስተዳደርና ልማት ትምህርት ክፍል መምህር ዋሲሁን በዛብህ፤ አሜሪካ የዓለም አቀፍ ህግ በመተላለፍ በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ጠንካራ እንዳይሆኑና  እንዲፈራርሱ ምክንያት መሆኗን በማንሳት አመላክተዋል።

በአሜሪካ ጣልቃ ገብነት የመፍረስ አደጋ ካጋጣማቸው ሀገራት መካከል አፍጋኒስታን፣ ሊቢያ፣ የመንና ሶሪያ ያነሱት ምሁሩ "ለሀገራቱ ሰላምና ደህንነት የምትጨነቅ በመምሰል ጣልቃ የገባችባቸው ሀገራት ፈራርሰዋል" ብለዋል።

ሀገራት እንዲገዙላት በተለያዩ መንገዶች የምታደርገው እጅ  ጥምዘዛ አልሳካ ካላት በማዕቀብ ለማንበርከክ እንደምትሞክር ነው የተናገሩት።

በኢትዮጵያ ላይም አልሳካ ያላትን ተላላኪ መንግስት የመፍጠር እቅድ በማዕቀብ ለማስገደድ እየሞከረች ቢሆንም እንደማይሳካላት ነው ምሁሩ የገለጹት።

በዚሁ ዩኒቨርስቲ የህግ ምሁሩ ጌታሁን ተሾመ በበኩላቸው፤ የአሜሪካ ጫና በትክክለኛ ምክንያት አልያም ባለማወቅ ሳይሆን የግል ጥቅሟን ለማስጠበቅ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

ከሰሞኑ ማዕቀብ ለመጣል ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የያዙት አቋም ፍጹም  ተገቢነት የሌለው አለም አቀፍ ህግን የተጻረረና ኢትዮጵያን የማዳከም ድብቁ ዓላማቸውን ያጋለጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት ጣልቃ ገብነቱን በመቃወም ልዕልናችንን ማስጠበቅ ይገባናል ነው ያሉት።

የዲፕሎማሲ ሥራውን ያለመታከት ማስቀጠል እንደሚገባ የተናገሩት ምሁሩ፤  " የነጩ ፖስታ ጎርፍ ለነጩ ቤተ መንግስት"  ዘመቻ በአሜሪካ  ብቻ ሳይወሰን  በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተጽዕኖ ፈጣሪ ለሆኑ ሀገራትም ጭምር መላክ እንዳለበት ጠቁመዋል።

አሜሪካ ለአሸባሪው ህወሓት በመወገን በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር ለፀጥታው ምክር ቤት በተደጋጋሚ ጊዜ ያቀረበችው ሃሳብ በአባል ሀገራቱ ውድቅ መደረጉን በማስታወስ አስተያየታቸውን የሰጡት ደግሞ የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል አስተባባሪ መምህር ጋድሴንድ ኮኖፋ  ናቸው።

ይህ አልሆን ሲል አለም አቀፍ ህግጋትን በተጻረረ መልኩ በራሷ ማዕቀብ ለመጣል የምታደርገው ሩጫ ከሽብርተኞች ጋር መተባበሯን የሚያመላክትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋን እምነት የሚያሳጣ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ጠንካራ መንግስት እንዳይገነባ ካላት ፍላጎት የተነሳ የራሷን ተላላኪ መንግስት ለመመስረት በቀጠናው ሴራ ስታሴር ቆይታለች ብለዋል።

ምሁሩ እንዳሉት፤ የአሜሪካን  ውሳኔ ሌሎች ሀገራት እንዲቃወሙ እንደማትፈለግ ሁሉ የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወሰነውን ውሳኔ አሜሪካ ልታከብረው ይገባል።

በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት የያዘው አቋም ጠንካራ መሆኑን የጠቆሙት ምሁሩ፤ የአሜሪካን ጣልቃ ገብነት መቃወሙ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም  ጭምር ፋይዳ እንዳለው በመረዳት በአቋሙ መጽናት አለበት ብለዋል።

ሌላው የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የህግ ምሁር ዳግም ወንድሙ፤ አሜሪካ ለጥቅሟ ስትል በሰብአዊ መብት ሰበብ በመግባት በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ላይ ማዕቀብ መጣሏን አስታውሰዋል።

በኢትዮጵያ ጉዳይ የሚወስነው በህዝብ የተወከለው ምክር ቤት እንጂ የአሜሪካ መንግስት ባለመሆኑ ከሽብርተኛ ቡድን ጋር ተደራደሩ ማለት ህገ-መንግስትን መፃረር ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያን ለመበታተን ብዙዎች ለዘመናት ቢሞክሩም  እንዳልተሳካላቸው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ በስነ-ልቦና በርትቶ አንድነቱን በማጠናከር የአሜሪካን ጣልቃ ገብነት ሊቃወም እንደሚገባ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም