በሶማሌ ክልል በተፈጠረው ግጭት ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ህክምና ተደርጎላቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል በተፈጠረው ግጭት ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ህክምና ተደርጎላቸዋል
አዲስ አበባ ነሀሴ 9/2010 በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በተፈጠረው ግጭት ጉዳት ለደረሰባቸው 207 ሰዎች የህክምና አገልግሎት መስጠቱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ። 79 ሰዎች ከባድ የቀዶ ህክምና ሲደረግላቸው 128 ለሚሆኑት ደግሞ የድንገተኛ የቀላል ህክምና እንደተሰጣቸው ገልጿል። በሚኒስቴሩ የሜዲካል ሰርቪስ ዳይሬክተር ጄነራል ዶክተር ዳንኤል ገብረሚካኤል ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከቅዱስ ጳውሎስ ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ፣ ከጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና ከየካቲት 12 ሆስፒታል የተውጣጡ 24 የህክምና ባለሙያዎችን የያዘ ቡድን ወደ ክልሉ ተጉዞ ለተጎጂዎች የህክምና አገልግሎት ሰጥቷል። እንደ ዶክተር ዳንኤል ገለጻ ፤ የህክምና አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ ጤና ተቋም መምጣት ያልቻሉ ተጎጂዎችን ለመርዳት በሚገኙበት ስፍራ በመሄድ ህክምናውን እንዲያገኙ ተደርጓል። በወቅቱ ከባድ የቀዶ ህክምና የተደረገላቸውና በጽኑ ህመም ውስጥ ያሉ ተጎጂዎችን ለመርዳት የኦክስጂን እጥረት ተከስቶ እንደነበር የገለጹት ዶክተር ዳንኤል ከመድኃኒት ፈንድ አቅርቦት ኤጀንሲ ጅግጅጋና ድሬዳዋ ቅርንጫፎች እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተለያዩ ሆስፒታሎች ኦክስጂን በመውሰድ የተጎጂዎችን ህይወት ማትረፍ መቻሉን ጠቁመዋል። በሚኒስቴሩ የተቋቋመው የህክምና ግብረ ኃይል ከሚሰጠው ህክምና ጎን ለጎን በግጭቱ ምክንያት የተዘጉ የጤና ተቋማት አገልግሎት እንዲጀምሩ መደረጉን ገልጸዋል። በተጨማሪም ተፈናቃዮች ባረፉበት መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ወረርሺኝ እንዳይከሰት የውኃ፣ የመድኃኒትና ሌሎች የህክምና ዕቃዎች ከመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጋር በመነጋገር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል። ሚኒስቴሩ የተጎጂዎችን ህይወት ለመታደግ ባደረገው ጥሪ የህክምና ባለሙያዎቹ በፈቃደኝነት ሙያዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ላሳዩት ትብብር ምስጋና አቅርቧል:: በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ህክምና ሲሰጡ የነበሩ የህክምና ባለሙያዎች አገልግሎታቸውን አጠናቀው ከትላንት በስቲያ አዲስ አበባ ተመልሰዋል። በክልሉ በተፈጠረው ግጭት በርካታ ሰዎችን ለህልፈተ ህይወትና ለአካል ጉዳት የዳረገ ሲሆን የንብረት ውድመትና ሃምሳ ሺህ ዜጎች ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል።