በኢትዮጵያ የኢኖቬሽን ባህልን ለማሳደግ ታስቦ በተዘጋጀ ፕሮግራም የሰለጠኑ ታዳጊ አምባሳደሮች ተመረቁ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የኢኖቬሽን ባህልን ለማሳደግ ታስቦ በተዘጋጀ ፕሮግራም የሰለጠኑ ታዳጊ አምባሳደሮች ተመረቁ
መስከረም 12/2014 (ኢዜአ) የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት በኢትዮጵያ የኢኖቬሽን ባህልን ለማሳደግ አልሞ ባዘጋጀው የኢኖቬሽን አምባሳደር ፕሮግራም ታዳጊ የኢኖቬሽን አምባሳደሮች ተመርቀዋል፡፡
በዕለቱ ለተማሪዎቹ የእውቅና እንዲሁም በሁዋዌይ አማካኝነት የተዘጋጀ የማበረታቻ ስጦታ ሲበረከትላቸው ተማሪዎቹ በቆይታቸው ማጠናቀቂያ የሰሯቸው ፕሮጀክቶች በእንግዶች ተጎብኝተዋል፡፡
በዝግጅቱ የቴክኖሎጂ እና ኦኖቬሽን ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር ኢ/ር ተሾመ ሳህለማርያም ቴክኖሎጂ ለአንድ ሀገር እድገት ወሳኝ ቢሆንም ከገበያ ገዝቶ ለመጠቀም አስቸጋሪና ከፍተኛ ወጪ ብሎም ዕውቀትን በመጠየቁ ከታችኛው ደረጃ አንስቶ ባሉት ተማሪዎች ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡
ለተመራቂ ተማሪዎቹም ኢኖቬሽንን በሄዳችሁበት ቦታ ሁሉ በማስተዋወቅና ወደፊትም በሰለጠናችሁበት ሙያ ችግር ፈቺ በሆኑ ምርምሮች ላይ ተሳትፋችሁ አኩሪ አስተዋፅዖ እንደምታደርጉ ከፍተኛ እምነት አለኝ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፕ/ር አፈወርቅ ካሱ ተማሪዎቹ ራዕይ እንዲኖራቸውና ያለንበት ጊዜ ምሁራን በብዛት የሚገኙበት እንደመሆኑም እነርሱን ተጠቅመው ራዕያቸውን እንዲያሳኩ ምክራቸውን ለግሰዋቸዋል፡፡
ሀገራችን አሁን ያለችበት ሁኔታ እኛን አይመጥነም ያሉት ፕ/ር አፈወርቅ ''የሰለጠናችሁትን ተጠቅማችሁ ሀገራችንን ወደተሻለ ደረጃ እንዲያሸጋግሩ ጠይቀዋል፡፡
የስቴም ፓወር የኢትዮጵያ ዳይሬክተሩ ዶ/ር ስሜነው ክሰከስ በበኩላቸው “ኢኖቬሽን ኢኮሲስተም ኢን ኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ በሀገራችንም ያለውን የኢኖቬሽን እንቅስቃሴ፣ ዕድል፣ ተግዳሮት፣ ፖሊሲ ብሎም ተቋማቸው ስቴም ፓወር ኢኖቬሽንን በማስፋፋትና የፈጠራ ባለሙያዎችን በመደገፍ ረገድ እየሰራ ስላላቸው ስራዎች ገለፃ አቅርበዋል፡፡
አክለውም እንደተቋም ለወደፊት ከተመራቂ ተማሪዎቹ ጋር ለመስራት ያላቸውን ፈቃደኝነት ገልጸዋል፡፡የተመረቁት ተማሪዎቹ በቀጣይ የኢኖቬሽን ባህልን የሚያስገነዝቡ ሁነቶችን በትምህርት ቤቶችና ሌሎች ማዘጋጃ ቦታዎች የማዘጋጀት፤ ሀገርና ዓለም አቀፍ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኩነቶች ላይ የሚሳተፉ እንዲሁም የኢኖቬሽን ባህል እንዲያድግ የሚሰሩ ይሆናል ተብሏል፡፡ምንጭ-የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት