በሰሜን የሃገሪቱ ክፍል መንግሥት በሃላፊነት ስሜት የሚያካሂደው የሰብዓዊ ድጋፍ ጥረት እውነቱ ሊሸፈን አይገባም - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን የሃገሪቱ ክፍል መንግሥት በሃላፊነት ስሜት የሚያካሂደው የሰብዓዊ ድጋፍ ጥረት እውነቱ ሊሸፈን አይገባም
መስከረም 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሰሜን የኢትዮጵያ ክፍል መንግሥት በሃላፊነት ስሜት የሚያካሂደው የሰብዓዊ ድጋፍ ጥረት እውነቱ ሊሸፈን እንደማይገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አስገነዘቡ።
አቶ ደመቀ በ76ተኛው የተ.መ.ድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ኒው ዮርክ አሜሪካ የገቡ ሲሆን፤ ከጉባኤው ጎን ለጎን ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ዴቪድ ባስሌይ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።
በውይይታቸው በሰሜን የሃገሪቱ ክፍል መንግሥት በሃላፊነት ስሜት የሚያካሂደው የሰብዓዊ ድጋፍ ጥረት መሬት ላይ ያለው እውነት ሊሸፈን እንደማይገባም አሳስበዋል። ሰብዓዊ ስጋቶችን ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ በዝርዝር ያስረዱ ሲሆን፤ በተደጋጋሚ የሰብዓዊ ድጋፍ አሰጣጥ ዙሪያ የሚገጥሙ ችግሮችን አብራርተዋል።
በሰብዓዊ ዕርዳታ ዙሪያ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍ ከአለም ምግብ ፕሮግራም ጋር መንግሥት በቅንጅት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በመጠቆም፤ በቀጣይም ውጤታማ በሆነ አግባብ ትብብሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የሰብዓዊ ድጋፍ አሰጣጥን በማመቻቸት ረገድ መንግስት ላይ ሚዛናቸውን ያልጠበቁ እና ትክክለኛ ያልሆኑ ክሶች ተደጋግመው እንደሚነሱ በማስታዎስ፤ በመንግስት በኩል የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ በችግሩ ተጎጂ ለሆኑ ወገኖች በሙሉ ተደራሽ ያደረገ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።