የአሸባሪው ህወሓት ወራሪ ኃይሎች አባቴን በቀበርኩ ማግስት እናቴን ገድለው አስከሬኗን በጅብ አስበሏት - ኢዜአ አማርኛ
የአሸባሪው ህወሓት ወራሪ ኃይሎች አባቴን በቀበርኩ ማግስት እናቴን ገድለው አስከሬኗን በጅብ አስበሏት

መስከረም 12/2014 (ኢዜአ) የአሸባሪው ህወሓት ወራሪ ኃይሎች አባቴን በቀበርኩ ማግስት እናቴን ገድለው አስከሬኗን በጅብ አስሏት በማለት እናቷ በግፍ የተገደለችባት አይሻ ሰይድ ትናገራች።
አይሻ ሰይድ ዳመነ የደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳ ቀበሌ-18 የገላና ጎጥ ነዋሪ ናት።
"የአሸባሪው ህወሓት ወራሪዎች አባቴን በቀበርኩ ማግስት ሃዘን ላይ የነበረች ደካማ እናቴን ገድለው አስከሬኗን ለጅብ በማስበላት ሃዘኔን እጥፍ ድርብ አድርገውብኛል" ትላለች።
አሸባሪው የህወሓት ወራሪ ኃይል ወረባቦ ወረዳን ለመቆጣጠር ባደረገው ሙከራ ቀበሌያቸውን በመውረር ከባድ ችግር ማድረሱን ትገልፃለች።
ወራሪው ኃይል አካባቢውን ለቀናት በተቆጣጠረበት ወቅት አባቷን ከቀበረች ሶስት ወር እንደነበረ የምትገልጸው አይሻ አካባቢያቸውን ትተው መሸሻቸውን ገልፃለች።
ይሁንና አቅም ያለው ሲሸሽ እናቷ ከአረመኔዎቹ የአሸባሪው ሃይሎች ማምለጥ እንዳልቻሉ ተናግራለች።"እናቴ ደካማ ስለሆነች ወደኋላ ቀረች፤ በባለቤቷ ሞት ሃዘን ላይ የነበረችውን ደካማ እናቴን ገድለውብኛል፤ ገድለዋትም ለጅብ አስበልተዋታል" ስትል በመሪር ኃዘን ገልፃለች።
እናቷን ከገደሏቸው በኋላም ስርዓተ ቀብራቸው እንዳይፈጸም በማድረግ 'ለጅብ እራት' እንዳደረጓቸው ተናግራለች።
የአሸባሪው ህወሓት ወራሪዎች ከአካባቢው በመውጣታቸው እናቷ የሚያሳድጓትን ህፃን ጨምሮ ስድስት የወንድሞቿንና የራሷን አንዲት ልጅ ይዛ ወደቤቷ መመለሷን ተናግራለች።
ወደቀያቸው ሲመለሱ አሸባሪዎቹ አንዳችም የሚቀመስ ነገር እንዳላስቀሩላቸውም ገልፃለች።
አይሻ መንግስት፣ ለጋሽ ድርጅቶችና ግለሰቦች ባዶ ቤት ቁጭ ብያለሁና ድጋፍ አድርጉልኝ ስትል ጠይቃለች።