በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በግጭት ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ እያደረጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በግጭት ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ እያደረጉ ነው
አዲሰ አበባ ነሀሴ 9/2010 በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ድጋፍና እንክብካቤ በማድረግ ላይ ናቸው። በአገር አቀፍ ደረጃ ከ13 ሚሊዮን በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በተያዘው የክረምት ወቅት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተሰማርተው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን እያገለገሉ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወጣት ታረቀኝ አብዱልጀባር ለኢዜአ እንደገለጸው፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረ ግጭት የተነሳ ለተፈናቀሉና ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸው። በጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ ድጋፍ እያደረጉ ያለው ከተለያዩ ተባባሪ አካላትና የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመሆን እንደሆነ ወጣት ታረቀኝ ጠቁሟል። ወጣቶቹ ለምግብነት የሚውሉ ግብአቶችን ጨምሮ አልባሳትና መሰል መሰረታዊ ቁሳቁሶችን በማሰባሰብ ለተፈናቃዮቹ በማከፋፈል ላይ መሆናቸውን ገልጿል። ተፈናቃዮቹን መልሶ ለማቋቋምና ወደቀያቸው ለመመለስ በሚደረገው ጥረትም ወጣቶቹ ተሳትፎ እያደረጉ ነው። በተለይም ወጣቶቹ በደቡብ ክልል ጌዴኦና ጉጂ አዋሳኝ አካባቢዎች እንደዚሁም በሶማሌ ክልል ከተፈጠረው ሁከት ጋር በተያያዘ ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍና ክብካቤ እያደረጉ ናቸው። እገዛ ከማድረግ ባሻገርም ህብረተሰቡ ከስሜታዊነት ባህርይ በመላቀቅ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የድርሻውን እንዲወጣ ለማስቻል በጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ ግንዛቤ የመፍጠር ተግባርም እያከናወኑ እንደሆነ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ገልጿል። የተፈናቀሉ ወገኖችን ከመርዳት ባሻገር ወጣት በጎ ፍቃደኞቹ በክረምት ትምህርት፣ በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ዙሪያ ግንዛቤ መፍጠር፣ በተፋሰስ ልማትና ችግኝ ተከላ እንዲሁም በመንገድ ትራፊክ ደህንነት አገልግሎቶች የተሰጣቸውን ኃላፊነትም እየተወጡ እንደሆነ ተገልጿል። የጎዳና ወጣቶች የስራ እድል የሚያገኙበትን ሁኔታ በመፍጠር እና ወደመጡባቸው የአካባቢዎች እንዲመለሱ የበኩላቸውን ድጋፍ እያደረጉ ሲሆን አረጋዊያንንም በመንከባከብ ላይ መሆናቸውን ወጣት ታረቀኝ ጠቁሟል። ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር በበኩሉ እየተከናወነ ላለው የበጎ ፈቃድ አገልገሎት ተባባሪ አካላት የሚያደርጉት እገዛም ለአገልግሎቱ ተደራሽነት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሆነ አመልክቷል። በሚኒስቴሩ የወጣቶች ማካተት፣ ንቅናቄና ተሳትፎ ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ማትያስ አሰፋ እንዳሉት፤ አገልግሎቱ ከመጀመሩ በፊት ከተባባሪ ተቋማት ጋር በአገልግሎቱ አሰጣጥ ዙሪያ ስምምነት ተደርጓል። ስምምነቱ በጎ ፈቃደኞቹ አገልግሎቱን ሲሰጡ ሁኔታዎችን ማመቻቸትና አስፈላጊውን እገዛ ማድረግን የሚያካትት ነው። በዚህም መሰረት ተባባሪ ተቋማቱ ወጣቶቹ አገልግሎቱን በይፋ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ለአገልግሎቱ የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ከማቅረብ ጀምሮ ክትትልና ድጋፍ እያደረጉ ናቸው። ይሁን እንጂ የግል እና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ለአገልገሎቱ እየሰጡት ያለው ድጋፍ ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰው ድንበር ተሻጋሪ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ኢትዮጵያ (Volentary Service Overseas Ethiopia) ድጋፍ እያደረጉ ስለመሆናቸው ጠቁመዋል። በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚደረገው እገዛ በመንግስት ተቋማት ብቻ የሚሸፈን ባለመሆኑ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችም ዘርፉን በመቀላቀል የድርሻቸውን እንዲወጡና ዜጎችን መልሶ ለሟቋቋም በሚደረገው ሂደት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።