የፀደይ ወር የተስፋ ምልክት እንደሆነ ሁሉ ወጣቶችም ለባህልና ለማህበረሰብ እድገት ተስፋ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የፀደይ ወር የተስፋ ምልክት እንደሆነ ሁሉ ወጣቶችም ለባህልና ለማህበረሰብ እድገት ተስፋ ናቸው
አዲስ አበባ መስከረም 11/2014 (ኢዜአ) የፀደይ ወር የተስፋ ምልክት እንደሆነ ሁሉ ወጣቶችም ለባህልና ለማህበረሰብ እድገት ተስፋ ናቸው ሲሉ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ከበደ ዴሲሳ ገለጹ።
"ቦራቲ አርት ፕሮሞሽን" ከኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር ከጳጉሜ 2/2013 እስከ መስከረም 11/2014ዓ.ም ከአዲስ አበባ እና ፊንፊኔ ዙሪያ በመጡ ፈቃደኛ ወጣቶች ሲከናወን የነበረው የሺኖዬና ጎቤ ፌስቲቫል ዛሬ በኦሮሞ ባህል ማዕከል ማጠቃለያውን አግኝቷል።
የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ዘርፈ ብዙ ውበት ያላቸው ልዩልዩ የዘመን መለወጫ ትውፊቶች አሏቸው።
ሽኖዬና ጎቤም በገዳ ስርዓት ውስጥ ከሚከወኑት የወጣቶች የዘመን መለወጫ ባህላዊ ትውፊቶች የሚካተቱ ናቸው።
ሽኖዬ በልጀገረዶች(ቀሬዎች) የሚከወን ሲሆን ጎቤ ደግሞ በወጣት ወንዶች ወይም ቄሮዎች የሚከወን ባህላዊ ጨዋታ(ጭፈራ) ናቸው።
ባህላዊ ትውፊቶቹ የዘመን መለወጫን የሚያበስሩ ሲሆኑ በውስጣቸው ያለፈውን ከማመስገን ባለፈ የፊቱን ብሩህ ዘመን መሻታቸውን የሚገልጹባቸውም ናቸው።
በልጀገረዶች(ቀሬዎች) የሚከወነው ሽኖዬ ጨዋታ እንደየአካባቢዎቹ ቁኒ ቡቅፈና፡ ቃሜ፣ እንግጫና የተለያዩ መጠሪያዎች ሲኖሩት፤ ጎቤም በተመሳሳይ በወጣት ወንዶች በየሰው ቤት እየተዞረ ከሳምንት በላይ የሚጨፈር ባህላዊ የዘመን መለወጫ ብስራት ነው።
ጎቤም እዮሼ ደሬና እዮሌ በመሳሰሉት ስሞች እንደየአካባቢው ይጠራል።
በዛሬው የፌቲቫሉ መዝጊያ የተገኙት የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ከበደ ዴሲሳ እንዳሉት የኦሮሞም ሆነ የብሔር ብሔረሰቦች ባህልና ወግ ለብዙ ዘመናት በሚፈለገው ደረጃ እንዲተዋወቅ ሳይደረግ ቆይቷል።
“አሁን አሁን ግን በህዝቡ በተለይም በወጣቶቹ ትግል የተደበቁት ባህሎችና ትውፊቶች አዳባባይ ወጥተው እየተንጸባረቁ ናቸው” ብዋል።
“ክረምቱ አልፎ የጸደይ ወር ሲገባ ኦሮሞ ብዙ በዓላት አሉት” ያሉት ሃላፊው፣ “ወራቱ ተስፋን እንደሚያሳዩ ሁሉ ወጣቱም ለባህሎቹ እድገትና ማህበረሰብ ንቃት ብሩህ ተስፋ ነው” ብለዋል።
“በመሆኑም በወጣቱና በማህበረሰቡ ጥንካሬ በዓላቱ እንዳይጠፉ ከመጠበቅ ታልፎ ዛሬ በዓለም አዳባባይ እየተንጸባረቁ ናቸው” ያሉት ሃላፊው ቄሮና ቀሬዎቹ ወጣቶችም እነዚህን ባህሎቻችን በጥሩ ስነ-ምግባር በማሳየታቸው እንደተደሰቱ ተናግረዋል።
የቦራቲ አርት ፕሮሞሽን ስራ አስኪያጅ አርቲስት ብሩክ ግርማ በበኩሉ “ዓላማችን ጎቤና ሺኖዬ የተባሉትን የወጣቶች የዘመን መለወጫ ትውፊቶቹን የኢትዮጵያና የአፍሪካ ወጣቶች መሰባሰቢያ መድረክ ማድረግ ነው” ብሏል።
በጭፈራው ላይ ያገኘናቸው ወጣቶችም ይኸን የዘመን መለወጫ የሆነውን ትውፊት ከማስተዋወቅና ለዓለም ከማንጸባረቅ አልፎ በኦሮሞና ሌሎች የከተማው ወጣቶች መካከል የአንድነትና የፍቅር መንፈስ ለማሳደግ ታስቦ ነው” ብለዋል።
ከቢሾፍቱ የመጣችው ወጣት ነዲ ሰለሞን እንዳለችው “ በዓሉ በገጠሩ አካባቢ ተወስኖ የቆየውን ባህላችንን ወደ ከተማው ማስፋትና ለዓለም ማስተዋወቅ ነው” ብላለች።
“ባህሉን ልክ እንደ ሌሎቹ የአገራችን በዓላት ማሳደግና የበለጠ ጎልቶ እንዲታይ ማድረግ ዓላማ አለን” ያለችው ደግሞ ከሰበታ የመጣችው ወጣት የውብዳር ልዑል ናት።
ሌላው ከዚሁ ከተማ የመጣው ወጣት አወቀ ተንኮሉም “ባህሉን ለዓለም ማስተዋወቅ ዋነኛው ዓላማችን ነው” ይላል።