ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያን የትኛውንም ጫና በጋራ ይመክታሉ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን የትኛውንም አይነት ጫና ለመመከት በጋራ ይቆማሉ ።

አሸባሪው ህወሃት ባለፉት 30 ዓመታት በህዝቦች መካከል መከፋፈልን እንዲፈጠር ከመስራቱ ባሻገር በኢትዮጵያውያን ላይ አስከፊ ግፍን ፈጽሟል።

አሸባሪ ቡድኑ ይህ አልበቃ ብሎት የሀገር ሉዓላዊ መገለጫ የሆነውን የመካለከያ ሠራዊት ላይ የክህደት ጥቃት በመፈጸም መንግስት ተገዶ ወደ ህግ ማስከበር ዘመቻ እንዲገባ አድርጓል።

መንግስት የትግራይ አርሶ አደሮች የመኸር እርሻ ተረጋግተው እንዲያከናውን በማሰብ  የተናጥል ተኩስ አቁም በማድረግ ሠራዊቱን ከትግራይ ክልል ቢያስወጣም አሸባሪ የህወሓት ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ በመፈጸም ሰላማዊ ዜጎችን እየጨፈጨፈ ይገኛል።

የአሸባሪ ቡድኑ ታጣቂዎች በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ሴቶችን ደፍረዋል፤ ነዋሪዎችንም ከሞቀ ቀያቸውና ከእርሻ ማሳቸው አፈናቅለዋል።

ነገር ግን "የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ነን" የሚሉ የምዕራባውያን ተቋማትና ሚዲያዎች ጉዳዩን በዝምታ እያለፉት ሲሆን፤ በተቃራኒው በመንግስት ላይ ጫና ለማሳደር እየጣሩ ነው።

የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በቅርቡ "በትግራይ ጦርነት ተሳታፊዎች ላይ ያነጣጠረ" በሚል አዲስ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ትዕዛዝ የፈረሙ ሲሆን፤ ይህም በዋናነት የአሸባሪውን ህወሃት ህልውና ለማራዘም ዓላማ ያደረገ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ቁጣቸውን እየገለጹ ነው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ ለአፍሪካ ሰላምና አንድነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገች ሀገር ናት።

በመሆኑም ኢትዮጵያን ማገዝ እንጂ ጫና መፍጠር ትክክለኛ አካሄድ አለመሆኑን ገልጸው፤ የኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ላይ የሚደረግ የትኛውንም አይነት ጫና ለመመከት በጋራ ይቆማሉ እንጂ አይንበረከኩም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያውያን ጫና በበዛ ቁጥር ይበልጥ አንድ የሚሆኑ ጠንካራ ህዝቦች መሆናቸውንም ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የገለጹት።

የኢትዮጵያ ታሪክ የሚያሳየውም ይህንኑ መሆኑን በመጠቆም።

አስተያየት ሰጪዎቹ አክለውም፤ ኢትዮጵያውያን ከመንግስት ጋር በመቀናጀት ሀገራቸው የያዘችውን እውነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳወቅ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

''ኢትዮጵያ አትፈርስም፤ ከእሷ በፊት እኛ ልጆቿ አለንላት'' በማለት ለሀገራቸው ህልውና እንደማይደራደሩም ነው የገለጹት።

"ኢትጵጵያ መርጣለች ፤ በመረጠቸውም መንግስት ትተዳደራለች" ያሉት አስተያየት ሰጭዎቹ ፤ ከዚህ አኳያ በመንግስት ላይ ጫና ለመፍጠር የሚደረግ ጥረት ኢትዮጵያውያን ላይ የተደረገ ጫና መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር የሚፈልጉ ሃይሎች ይህን መገንዘብ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም