ቀጥታ፡

አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ወጣቶችን በሁሉም መስክ አሳታፊ ማድረግ አለበት

አዲስ አበባ መስከረም 11/2014  አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ወጣቶችን በሁሉም መስክ አሳታፊ ማድረግና ለሥራ እድል ፈጠራም ልዩ ትኩረት መስጠት አለበት ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣቶች ተናገሩ።

በመጀመሪያው ዙር ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው ውጤት መሰረት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብልጽግና ፓርቲ 410 ወንበር አግኝቷል።

በኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 56 መሰረት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ ድርጅቶች የፌደራሉን መንግስት የሕግ አስፈጻሚ አካል ያደራጃል /ያደራጃሉ (ይመራል/ይመራሉ) ይላል።

በዚሁ መሰረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 547 መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን፤ በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ 410 ወንበር በማግኘት መንግስት መመስረት የሚያስችለው መሆኑ ተረጋግጧል።

በመሆኑም መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም የአዲስ መንግስት ምስረታ እንደሚካሄድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማሳወቁ የሚታወስ ነው።

በኢትዮጵያ ወጣቶች የሚባሉት ከ15 እስከ 29 ባለው የእድሜ ክልል የሚገኙ ሲሆን፤ በዚሁ መስፈርት መሰረት በኢትዮጵያ ከ30 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች እንደሚገኙ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ ያመለክታል።

ኤጀንሲው ከዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ጋር እ.አ.አ በ2021 ባደረጉት የዳሰሳ ጥናት በኢትዮጵያ ከሚገኙ ወጣቶች 16 ሚሊዮን 930 ሺህ 649 ለሥራ ዝግጁ የሆኑና ሥራ የሚፈልጉ ወጣቶች ናቸው።

ለስራ ዝግጁ ከሆኑት ወጣቶች መካከል ደግሞ 1 ሚሊዮን 998 ሺህ 472ቱ ሥራ አጥ ሲሆኑ በኢትዮጵያ ለስራ ዝግጁ ከሆኑ 100 ወጣቶች መካከል 12ቱ ሥራ-አጥ ናቸው ማለት ነው።

ኢዜአ አዲስ ከሚመሰረተው መንግስት ምን ይጠብቃሉ? በሚል ያነጋገራቸው ወጣቶች መካከል ወጣት አቤል አስራት ወጣት ፍራኦል አለማየሁ ናወጣት ቆንጂት ሽረታ አዲሱ መንግስት ብዙ የቤት ሥራዎች አሉበት ከእነዚህ ውስጥ ዋነኛው የሥራ እድል ፈጠራ ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል።

"በርካታ ወጣቶች ተመርቀው ሥራ አላገኙም" ያሉት ወጣቶቹ አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ለሥራ እድል ፈጠራ ትኩረት መስጠት አለበት ብለዋል።

መንግስት የሥራ እድል የሚፈጥርባቸውን መስኮች በማስፋት አዳዲስ ዘርፎችን ማካተት እንደሚገባውና ወጣቱ ሥራ ለመፍጠር የሚያስችለውን የአሰራር ሥርዓቶች መዘርጋት ይጠበቅበታል ብለዋል።

ከሥራ እድል ፈጠራ ጋር ያሉ የአሰራር ማነቆዎችን በመፍታት ወጣቱ ቀልጣፋ አገልግሎት የሚያገኝበትን ሁኔታ ሊያመቻች ይገባልም ነው ያሉት።

ወጣቱ በኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት ውስጥ ካለው ድርሻ አኳያ አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ወጣቶችንና ሴቶችን በፖለቲካው መስክ አሳታፊ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል።

አዲስ የሚመሰረተው መንግስት የኢትዮጵያን ሰላምና የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ዋነኛ ትኩረቱ አድርጎ መሥራት እንደሚጠበቅበትም ገልጸዋል።

መንግስት የሕግ የበላይነትን ማስከበር ከቻለ በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋትን ማምጣት ይቻላልም ነው ያሉት።

በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት የማቋቋም ሥራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ያሉባትን የውጭ ጫናዎች ተቋቁማ ሉዓላዊነቷንና አንድነቷን ማስጠበቅ አለባት ያሉት ወጣቶቹ፤ ለዚህ አገራዊ ኃላፊነት የሚመጥን ጠንካራ መንግስት ሊመሰረት ይገባል ብለዋል።

ሕዝብ በሰጠው ድምጽ የሚመሰረተው መንግስት ሕዝቡ ምን ይፈልጋል? ለሚለው ጉዳይ ትኩረት በመስጠት በአገልጋይነት መንፈስ መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ፣ የጌዲኦ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲና የግል እጩ ተወዳዳሪዎች ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ አግኝተዋል።

ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በተለያዩ ምክንያቶች ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም ምርጫ የሚካሄድ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም