ቀጥታ፡

መጪውን የመስቀል በዓል በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ተጠናቋል--የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን

አዲስ አበባ መስከረም 11/2014 መጪውን የመስቀል በዓል በድምቀት ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት አስታወቀ::
የቤተክህነቱ ምክትል ስራ አስኪያጅ ሊቀ አዕላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን በበዓሉን አከባበር አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ተገቢውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የጥንቃቄ መመሪያ ተግባራዊ በማድረግ  በዓሉን በድምቀት ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት ተከናውኗል ነው ያሉት።

በዓሉ ያለምንም ፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የመስቀል አደባባይ ግንባታ ፕሮጀክት እጅግ ማራኪ በሆነ የግንባታ ገጽታ መጠናቀቁን አስታውሰው፤ ይህም የዘንድሮውን በዓል ልዩ ድምቀት ይፈጥርለታል ብለዋል።

ቤተክርስቲያኗ ኮሚቴ በማዋቀር የመስቀል በዓል በድምቀት እንዲከበር እየሰራች መሆኑንም ነው ያነሱት።

ምዕመናኑ በዓሉ በሰላም እንዲከበር የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም የቤተክህነቱ ምክትል ስራ አስኪያጅ ሊቀ አዕላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም