"የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ሰራዊቱ ሁሌም ዝግጁ ነው" - ኢዜአ አማርኛ
"የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ሰራዊቱ ሁሌም ዝግጁ ነው"
አዲስ አበባ፣ መስከረም 11/2014 (ኢዜአ) "የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ሰራዊቱ ሁሌም ዝግጁ ነው" ሲሉ የአገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖች ተናገሩ።
ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የአገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖች ህብረተሰቡ እያደረገ ያለው ድጋፍና ጠንካራ ደጀንነት ለሰራዊቱ ከፍተኛ ሞራል ሆኖታል ብለዋል።
ከመኮንኖቹ መካከል ሻለቃ ቴዎድሮስ ተስፋሁን፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ለአገሩ የማይከፍለው ዋጋ የለም፤ የቁርጥ ቀን የሚሆኑ በርካታ ጀግኖች ያሏት አገር መሆኗንም ማንም ያውቀዋል ብለዋል።
"የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ሰራዊቱ ሁሌም ዝግጁ ነው" ሲሉም አረጋግጠዋል።
የህዝቡ ድጋፍና እገዛ ሁላችንንም ያኮራ፤ ለአገራችን ክብርና ሉአላዊነት ስንል በቆራጥነት እንድንቆም ተጨማሪ ሃይል ሆኖናል ያሉት ደግሞ ከሰራዊቱ አመራሮች መካከል ሻለቃ ኤልያስ ማሞ ናቸው።
በተለያዩ መልኩ የሚደረጉት ድጋፎች ሠራዊቱን ለበለጠ ድል የሚያነሳሱ ናቸው ሲሉም ተናግረዋል።
የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ግንባር ድረስ በመገኘት እያደረጉት ያለው የሞራል ግንባታ ስራ፣ የማህበረሰቡ ሁሉን አቀፍ ድጋፍና እገዛ አኩርቶናል ያሉት ደግሞ ሻምበል ጥላሁን መልካሙ ናቸው።
"ኢትዮጵያዊያን ድጋፋቸውን አጠናክረው ይቀጥሉ፤ እኛም ለአገራችን ክብርና ሉአላዊነት ሁሌም አለን" ሲሉ መኮንኖቹ አረጋግጠዋል።