ቀጥታ፡

የባህልና ቱሪዝም ዘርፎች ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ

መስከረም 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) የባህልና ቱሪዝም ዘርፎች ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው ጥሪ አቀረቡ።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አዘጋጅነት "እግር ኳሳችን ለሰላማችን" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍና የምስጋና መርሃ ግብር ተካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው፤ አገርን ለማዳን እየተደረገ ባለው ዘመቻ የባህልና ቱሪዝም፣ የኪነ-ጥበብና ስፖርት ዘርፎች እያደረጉት ያለውን አስተዋጽኦ አብራርተዋል።

በቀጣይም ስፖርት ለሰላም ያለውን አስተዋጽኦ በማጠናከር ሌሎች የባህልና ቱሪዝም ዘርፎች ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፌደሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ የአገር አንድነትንና ሰላም ለማስጠበቅ በሚደረግ ዘመቻ የስፖርት ቤተሰቡ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል።

እስካሁን 16 የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች አጠቃላይ ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸው፤ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የመከላከያ ሰራዊት ኢንዶክትሪኔሽን ዳሬክቶሬት ተወካይ ብርጋዴል ጀነራል አስፋው ማመጫ፤ ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ያላቸው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል።

ህዝቡ ለሰራዊቱ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ጠንካራ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

“በቀደምት አባቶች መስዋትነትና ተጋድሎ ለአለም ጥቁር ህዝቦች ተምሳሌት ሆና የኖረችን አገር በነበረችበት ክብሯ ለማስቀጠል ሰራዊቱ ሁሌም ዝግጁ ነው” ሲሉም አረጋግጠዋል ።

"ኢትዮጵያ በማንም የምትፈርስ አገር አይደለችም፤ ማንም አጉራ ዘለል ተነስቶ የሚንዳት አገርም አይደለችም፤ ሁሌም ለክብሯ የሚቆሙ ጀግኖች ልጆች አሏት" ሲሉም ተናግረዋል ብርጋዴል ጀነራል አስፋው።

በኢትዮጵያ የድል ታሪክ ስፖርትና ኪነ-ጥበብ የነበራቸውን አስተዋጽኦ በማውሳት አሁን እየተደረገ ባለው የህልውና ዘመቻ የዘርፉን አበርክቶ ታሪክ እንደማይዘነጋው ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ለሰራዊቱ ገቢ የሚሆን የስዕል ጨረታም ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም