“አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት ከአገር አፍራሾቹ ህወሓትና ሸኔ በስተቀር ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር አብሮ ይሰራል የሚል እምነት አለኝ”... የኢዜማ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ - ኢዜአ አማርኛ
“አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት ከአገር አፍራሾቹ ህወሓትና ሸኔ በስተቀር ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር አብሮ ይሰራል የሚል እምነት አለኝ”... የኢዜማ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2014(ኢዜአ) አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት ከአገር አፍራሾቹ ህወሓትና ሸኔ በስተቀር ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር አብሮ ይሰራል የሚል እምነት አለኝ ሲሉ የኢዜማ ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ አስታወቁ።
አቶ ግርማ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት አገር ለማፍረስ ቆርጠው ከተነሱ ሀይሎች በስተቀር የተለያየ አመለካከት ካላቸው የፖለቲካ ኃይሎች ጋር መወያየትና አብሮ መስራት ለአገሪቱ መጻዒ ዕድል ወሳኝ ነው፡፡
ለአገር አድነትና ዘላቂ ሰላም ሲባል የተለያየ አመለካከት ቢኖራቸውም ስለ አገራቸው ተቆርቋሪ ከሆኑ ኃይሎች ጋር መወያየትና በሀገሪቱ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ እና ወሳኝ እንዲሆኑ ማድረግ ለአገሪቱ መጻዒ ዕድል ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
አቶ ግርማ እንዳሉት በዚህ በጭንቁ ጊዜ የተለያየ አመለካከት ያላቸው ፓርቲዎችም ሆነ ቡድኖች አገሪቱን ከተደቀነባት አደጋ ለመታደግ ያለምንም አመለካከት ልዩነት በጋራ ቆመው መመከታቸው በታሪክ መዝገብ በደማቅ ቀለም የሚጻፍና ሊበረታታ የሚገባ ነው፡፡
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ አገር ለማፍረስ አቅደው እየሰሩ ያሉ አሸባሪዎቹ ህወሓት ና ሸኔ ኃይሎች ጋር ድርድር ማድረግ እንደማያስፈግ ነገር ግን ከእብደታቸው ታቅበው ለፈጸሙት ጥፋት ተጠያቂ የመሆን ፊላጎት ካላቸው፤ እንዲሁም ወንጀለኞችን አሳልፈው የሚሰጡ ከሆነ ነገሮችን በጥልቀትና በብስለት ማየት አይከፋም ሲሉም ተናግረዋል።
ከውይይት በተጨማሪ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ልማት ማስፈን በዋነኝነት የመንግስት ኃላፊነት መሆኑን የገለጹት አቶ ግርማ፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የነበሩ ክፍተቶችን በዚህ በጭንቁ ጊዜ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከመፎካከርና ከመነቋቆር ይልቅ አለመግባባቶችን ወደ ጎን በመተው እንደ ወትሮው በተባበረ ክንድ አገር ለማዳን የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አሸባሪው ህወሓት “ኢትዮጵያን ካላፈረስኩ ከድርጊቴ አልታቀብም” እያለ ባለበት በዚህ ወቅት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ የተናገሩት አቶ ግርማ፤ መንግሥትም ህዝቡን በሚገባ በማስተባበር ሀገሪቱ ሳትወድ የገባችበትን ጦርነት በአጭር እንዲቋጭ ማድረግ አለበት ሲሉም ጠቁመዋል፡፡
ጦርነቱ በረዘመ ቁጥር በይበልጥ የሚጎዳው የትግራይ ክልል ህዝብን ነው ያሉት አቶ ግርማ፣ የትግራይ ህዝብ ጦርነቱ እንዲቋጭ አሸባሪው ህወሓት ላይ ግፊት ማድረግ እንዳለበትና መላው የኢትዮጵያ ህዝብም ያለምንም የፖለቲካ፣የሃይማኖትና የዘር ልዩነት በጋራ በመቆም የተጀመረውን አገር የመታደግ ዘመቻ ዳር እንዲያደርስ ጥሪ አቅርበዋል፡፡