የምግብ ዘይት በቅናሽ ዋጋ እየቀረበልን ነው - የደብረ ማርቆስ ነዋሪዎች

ደብረ ማርቆስ ፡መስከረም 11/2014 (ኢዜአ) በአካባቢያቸው የምግብ ዘይት በቅናሽ ዋጋ እንደቀረበላቸው  በምስራቅ ጎጃም ዞን የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

በደብረ ማርቆስ ከተማ የተገነባው የደብሊው ኤ ዘይት ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ  በበኩላቸው፤ ፋብሪካው   የሙከራ ስራውን አጠናቆ  ማምረት በመጀመሩ በሀገሪቱ የተፈጠረውን የምግብ ዘይት የዋጋ ንረት ለማረጋጋት እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ነዋሪዎቹ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በከተማዋ የተገነባው የምግብ ዘይት ፋብሪካ ምርት አምርቶ ለገበያ ማቅረብ በመጀመሩ በቅናሽ ዋጋ ገዘተው መጠቀም ጀምረዋል።

ከከተማ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ  ጤናየ ድንቁ በሰጡት አስተያየት፤ የፋብሪካውን የምግብ ዘይት  ምርት በሸማቾች ህብረት ሰራ ማህበራት አማካኝነት እየቀረበላቸው  ገዝተው መጠቀም  መቻላቸውን ተናግረዋል።

ሌሎች የዘይት ምርቶችን  ባለ 5 ሊትር በ670 ብር ገዝተው መጠቀማቸውን አስታውሰው፤ አሁን ግን ከደብሊው ኤ ዘይት ፋብሪካ በ465 ብር በመግዛት መጠቀም እንደቻሉ ገልጸዋል።

ይህም  በ205 ብር ቅናሽ  ያለው በመሆኑ እየተጋነነ የመጣውን የምግብ ዘይት ዋጋ ማረጋጋት ያስችላል ብለዋል።

አስተያየት ሰጪዋ እንዳሉት፤ፋብሪካው የህብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ያደረገው የዋጋ ቅናሽ  ፋብሪካው የህዝብ መሆኑን በተግባር ያሳየበት ነው።

 የ"ደብሊው ኤ " የዘይት ፋብሪካ ምርት በወሳኝ ጊዜ ላይ  የደረሰ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ንጹህ አደራው ናቸው።

ዋጋው   የገቢ አቅማቸውን ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን የጠቆሙት ወይዘሮ ንጹህ  ፤ የዘይቱ የጥራት ደረጃም ከሌሎች ምርቶች የተሻለ ሆኖ እንዳገኙት አስረድተዋል።

በከተማዋ የቀበሌ ሁለት ሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር አባል ወይዘሮ ዞማ ታደለ ፤  ዘይቱ በቅናሽ ዋጋ መሸጥ መጀመሩ ተጠቃሚ እንድሆን አድርጎኛል ብለዋል።

 በአነስተኛ ገቢ እንደሚተዳደሩና  የምግብ ዘይት ዋጋ መጨመር በኑራቸው ላይ ጫና ፈጥሮ እንደቆየ ጠቅሰው፤ አሁን ላይ የፋብሪካውን ምርት አንድ ሊትር ዘይት በ93 ብር በመግዛት መጠቀም እንደቻሉም ተናግረዋል።

የደብሊው ኤ ዘይት ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር አዮብ ወረታው  ፤ ፋብሪካው በቀን ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሊትር የማምረት አቅም እንዳለው ጠቅሰው፤ የሙከራ ስራውን አጠናቆ ማምረት በመጀመሩ በሀገሪቱ የተፈጠረውን የምግብ ዘይት የዋጋ ንረት ለማረጋጋት ማገዝ ጀምሯል ብለዋል።

አሁን ላይ በፋብሪካው የተመረተ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር ለአካበቢው ማህበረሰብ ማቅረብ መጀመሩን ጠቅሰው፤ በቀጣይ በብዛትና በጥራት  በማምረት ወደ ሌሎች የሀገሪቱ አካካቢዎች ማቅረብ እንደሚጀምር አስታውቀዋል።

አሁን ባለው የገበያ ዋጋ በሊትር ከ50 እስከ 70 ብር ቅናሽ በማድረግ ማቅረብ መጀመሩን አስረድተዋል።

የዘይት ምርቱ በተቋማት ተደራጅተው በሚመጡና በሸማቶች ህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት ለተጠቃሚው ማህበረሰብ እንዲደርስ እየተደረገ ነው ያሉት ስራ አስኪያጁ።

እንደ ሀገር የተፈጠረውን የምግብ ዘይት አቅርቦት ችግር ለማቃለል በትኩረት  እየተሰራ መሆኑንም አመላክተዋል።

የደብሊው ኤ ዘይት ፋብሪካ በሀገር ውስጥ ባለሀብቱ አቶ ወርቁ አይተነው በ5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ተገንብቶና በቅርቡ ተመርቆ ወደ ሙከራ ምርት መግባቱ በወቅቱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም