ቀጥታ፡

የሽብር ቡድኑን በመደምሰስ ታሪክ ለመስራት ተዘጋጅተናል

ደሴ፣ መስከረም 11/2014 (ኢዜአ) በህዝባችን ላይ ግፍና ሰቆቃ እየፈፀመ ያለውን አሸባሪ የህወሓት ቡድንን ከሠራዊቱ ጎን ተሰልፈን በመደምሰስ ታሪክ ሰርተን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ተዘጋጅተናል ሲሉ የደቡብ ወሎ ዞን ወጣቶች አስታወቁ።

የሐይቅና የተሁለደሬ ነዋሪ ወጣቶች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ በሐይቅ ከተማ መክረዋል።

በምክክር መድረኩ ከተሳተፉት መካከል የሐይቅ ከተማ ነዋሪ ወጣት አደም የሱፍ በሰጠው አስተያየት፤ አሸባሪው የህወሓት ቡድን  ኢትዮጵያን ለማፍረስ መኖሪያ ከተማቸው ድረስ መጥቶ ለመውረር መሞከሩን  አስታውሷል።

ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በመቀናጀት እስከ ህይወት መስዋዕትነት ጭምር ተከፍሎ የጥፋት ቡድኑን አሳፍረው መመለሳቸውን ተናግሯል።

"የአባቶቻችንን የቆየ ታሪክ አበላሽቶ በህዝባችን ላይ ግፍና ሰቆቃ ለመፈጸም የመጣን ወራሪ ኃይል ደምስሰን ታሪክ ለመስራት ቆርጠን ተነስተናል" ብሏል።

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በዘላቂነት ለማስጠበቅ መከላከያ ሠራዊትን ለመቀላቀል መወሰኑንም ነው ወጣቱ  የገለጸው።

ሌላው የተሁለደሬ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ኤርሚያስ አሊ ''እኛ ወጣቶች እያለን ሀገር በጠላት ተወራ ሉዓላዊነቷ አይደፈርም'' ብሏል።

"አሸባሪው ቡድን የሚፈጽመውን ግፍና ስቃይ እያዩ ማለፍ አይቻልም'' ያለው ወጣቱ፤ ከሠራዊቱ  ጋር በመሆን ቡድኑን በመቅበር ታሪክ ለመስራት መነሳሳቱን  ተናግሯል።

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እንዲጠበቅ እስከ ህይወት መስዋዕት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑንም አስታውቋል።

የክልሉ ወጣት ከሠራዊቱ ጋር ተቀናጅቶ የጥፋት ቡድኑን እየተፋለመ መሆኑን የገለጸው ደግሞ የአማራ ክልል ወጣቶች ማህበር ፕሬዚዳንት አባይነህ ጌጡ ነው።

"ቡድኑ  አማራን አዋርዶ አንገት በማስደፋት ኢትዮጵያን የማፍረስ ከንቱ ምኞትና ቅዥት ማክሸፍ ከሁላችንም ይጠበቃል" ሲል ተናግሯል።

"ጀግኖች አባቶች በደምና አጥንታቸው ነጻነቷንና ሉዓላዊነቷን ጠብቀው ያቆዩንን ሀገር በተራችን የመጠበቅ ኃላፊነታችንን እንወጣለን" ብሏል።

"ሐይቅ ከተማን ለመዝረፍና ለማውደም አሰፍስፎ የመጣውን ወራሪ ኃይል በቅንጅት እንደቀበርነው ሁሉ በሌሎችም የአካባቢዎች ዘው ብሎ በገባበት ሁሉ እንዲቀበር ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት አለብን" ያሉት ደግሞ የሐይቅ ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ ከበደ ካሣ ናቸው።

አሰፍስፎ የመጣውን ጠላት ወጣቶች እስከ ህይወት መስዋዕት በመክፈል ታሪክ መስራታቸውን ገልጸዋል።

"ወጣቱ ስልጠና ወስዶ የሀገሩን ሉዓላዊነት በዘላቂነት እንዲጠብቅ መከላከያና ልዩ ኃይሉን እንዲቀላቀል እየሰራን ነው" ብለዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች ሊግ ኃላፊ ወይዘሮ መሰሉ ብርሃኑ በበኩላቸው "አንድነታችንን ጠብቀን ኢትዮጵያን ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች የምንጠብቅበት ወቅቱ አሁን ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

የሽብር ቡድኑን ግፍና በደል በማስቆም ዳግም ስጋት እንዳይሆን ለማድረግ ሁሉም ከፀጥታ መዋቅሩ ጎን ተሰልፎ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል።

በምክክር መድረኩ  የክልል፣ ዞን፣ ተሁለደሬ ወረዳና ሐይቅ ከተማ አመራሮች፣ ወጣቶችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም