ኢትዮጵያ ክብሯን ለመድፈር የሚቅበዘበዙትን አደብ የሚያስገዙ ጀግኖች አጥታ አታውቅም - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ክብሯን ለመድፈር የሚቅበዘበዙትን አደብ የሚያስገዙ ጀግኖች አጥታ አታውቅም
መስከረም 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) "ኢትዮጵያ ክብሯን ለመድፈር የሚቅበዘበዙትን ሁሉ አደብ የሚያስገዙ ጀግኖች አጥታ የማታውቅ ታላቅ አገር ናት " ሲሉ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ገለጹ።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በ2013 ዓ.ም በጀት የእቅድ አፈጻጸምና የ2014 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች አስመልክቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ያዘጋጀው የውይይት መድረክ ዛሬ ተጀምሯል።
ከውይይቱ ጎን ለጎንም የኢትዮጵያ ከተሞች "የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግሥት" ዘመቻን ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሀመድ አስጀምረዋል።
"ሁሉም ኢትዮጵያዊ የኢትዮጵያ አምባሳደርና ጠበቃ በመሆን የአገራቸውን እውነት ለዓለም የሚያሳዩበት ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን" ያሉት ኢንጂነር አይሻ፤ "የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግሥት ዘመቻ የኢትዮጵያን እውንት ለዓለም አቅፉ ማህበረሰብ ከምናሳውቅባቸው መንገዶች አንዱ ነው" ብለዋል።
ኢትዮጵያን ለማፍረስና ለማዳከም የሚሯሯጡ ጠላቶቿ ህብረት ፈጥረው አገሪቷ እንዳታድግና እንዳትለማ እየሰሩ መሆናቸው ገሃድ መውጣቱን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ አሁን የገጠሟትን ፈተናዎች በድል ተወጥታ ወደ ሚመጥናት ከፍታ የጀመረችውን ጉዞ እንደምትቀጥል የሚያጠራጥር ጉዳይ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት ሠራተኞች ለአገር መከላከያ ሠራዊትና ለሕልውና ዘመቻው እያደረጉ ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመልክተዋል።