ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ ለኤርትራውያን ስደተኞች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

መስከረም 10/2014 (ኢዜአ)፡ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ለኤርትራውያን ስደተኞች ድጋፍ እንዲያደርግ አዲስ አበባ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ጠየቁ።

ትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ ስደተኞቹን ለማስወጣት ባለመቻሉ ስጋት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።
 ኮሚሽኑ በበኩሉ በስደተኞቹ ጉዳይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ገልጿል።

ስደተኞቹ ዛሬ በአዲስ አበባ የኮሚሽኑ የኢትዮጵያ ወኪል ቢሮ ደጃፍ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል።

ስደተኞቹ እንደሚሉት፤ ባለፉት ሁለት ወራት በትግራይ ክልል በተለይም ህንጻጽና ማይ-አይኒ የተባሉ የስደተኛ መጠለያዎች ለሚገኙ ኤርትራውያን ድጋፍ እየቀረበ አይደለም።

በመጠለያ ካምፖቹ የምግብ፣ የውኃ፣ የህክምና የመድሃኒት አቅርቦት ባለመኖሩ ስደተኞቹ ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን ተናግረዋል።

በተለይም የተለያየ የጤና ችግር ያለባቸው ስደተኞች በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ የስቃይ ጊዜ እያሳለፉ መሆኑንም ገልጸዋል።

በመሆኑም ኮሚሽኑ ስደተኞችን የሚያስተናግድበትን ሕግ አክብሮ አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ነው ያሉት።

ስደተኞቹ አክለውም ከዚህ ቀደም ትግራይ ክልል ያሉትን ስደተኞች ወደ ሰሜን ጎንደር ዳባት ለማስወጣት ታቅዶ እንደነበር አስታውሰዋል።

ኮሚሽኑ ስደተኞቹን ለማስወጣት ምንም እንቅስቃሴ እያደረገ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ለስደተኞቹ ሌላ ስቃይ እንደሆነ አንስተዋል።

ክልሉን ተቆጣጥሮ የሚገኘው አሸባሪው ሕወሓትም በስደተኞች ላይ የተለያዩ በደሎችን እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን የኢትዮጵያ ተወካይ ማማዱ ዲያን ባልዴ በበኩላቸው፤ በችግሩ መፍትሄ ዙሪያ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

''ከወኪሎቻችሁ ጋር ተነጋግረናል፤ ያለውን ችግርና ስቃይ እንረዳለን፣ ወደ ሌላ ቦታ ማስፈሩንም እያሰብንበት ነው'' ብለዋል።

በተመሳሳይ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አስተዳደር ኤጀንሲ ባወጣው መግለጫ በትግራይ የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞችን ጎንደር ዳባት በሚገኝ 'አለም ዋች' ወደ ተባለ ጣቢያ ለማዘዋር እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

እንደኤጀንሲው ገለጻ በ91 ሔክታር መሬት ላይ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ግንባታ እይተከናወነ ይገኛል።

እስካሁንም ኤጀንሲው አሸባሪው ሕወሓት ማይአይኒና አዲ ሃሩሽ የተባሉ መጠለያዎች ከማጥቃቱ በፊት ወደ ዳባት የመጡ 227 ስደተኞችን እየተንከባከበ መሆኑንም ገልጿል።

በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ7 እስከ 8 ሺህ የሚሆኑ ስደተኞችን ለማዛወር በዳባት ወረዳ አራት ትምህርት ቤቶችና ሶስት ማሰልጠኛ ካምፖች እየተዘጋጁ መሆኑም አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም