የአሜሪካን መንግስት ተጨማሪ ማዕቀብ የኢትዮጵያን እውነታ ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአሜሪካን መንግስት ተጨማሪ ማዕቀብ የኢትዮጵያን እውነታ ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው
ዲላ፤ መስከረም 10/2014 (ኢዜአ)፡ የአሜሪካን መንግስት ተጨማሪ ማዕቀብ የመጣል መነሳሳት የኢትዮጵያን እውነታ ከግምት ውስጥ ያላስገባ ፍትሃዊነት የጎደለው መሆኑን በጌዴኦ ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ ።
አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ እጥለዋለሁ የምትለው ተጨማሪ ማዕቀብ መንግስት በሆደ ሰፊነት ሲያደርግ የቆየውን ታጋሽነትና ጥረት ከግምት ውስጥ ያላስገባ መሆኑን ነው ነዋሪዎቹ ጉዳዩን አስመልክተው ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የገለጹት።
በዞኑ የዲላ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ባለሃብት አቶ አበበ ቢራራ እንዳሉት፤ አሜሪካ በፌዴራል መንግስትና በአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች፤ በኤርትራ መንግስት ባለስልጣናት ማዕቀብ እንዲጣል መነሳሳቷ ፍትሃዊነት የጎደለው ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት የተናጠል ተኩስ ማቆምን ጨምሮ በተደጋጋሚ ለሰላም ያሳየውን ትእግስትና በህግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጣርተው እርምጃ እንዲወሰድ እያደረገ ያለውን ጥረት ከግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም ብለዋል።
በመንግስትና ህዝብ ቅንጅት በሀገር ህልውና ላይ የተጋረጠን አደጋ ለመመከት እና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚከናወነውን ስራ ከአሸባሪው የህወሓት ቡድን ጥቃት እኩል መመልከት ፍትሃዊነት የጎደለው መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በሀገራችን ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ለመጣል መነሳሳታቸው የኢትዮጵያን እውነታ ከግምት ውስጥ ያላስገባ ፍትሃዊነት የጎደለው መሆኑን የገለጹት አቶ አበበ፤ በዚህ ሳንበገር ኢትዮጵያውያን የሽብር ቡድኑንን የማጥፋት ጥረታችንን አጠናክረን መቀጠል አለብን ነው ያሉት።
የዲላ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪና የቀድሞ ጦር ሰራዊት አባል አስር አለቃ ሲሳይ ገብሬ በበኩላቸው ፤ ህውሓት አለም አቀፍ የጦር ህግጋትንና የሰብዓዊ መብት ክልከላዎችን በመጣስ ወንጀል የፈጸመ አሸባሪ ቡድን መሆኑን ተናገረዋል።
ከሽብር ቡድኑ ጋር በአስቸኳይ ወደ ድርድር ካልገባቹ ማዕቀብ እጥላለሁ የሚለው የአሜሪካ ማስፈራሪያ የሀገራችንን ሉአላዊነት የሚጋፋ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
ህውሓት መከላከያ ሰራዊትን ከጀርባው በመውጋት ጦርነት እንዲቀሰቀስ ምክንያት መሆኑን ያስታወሱት ፤ አስር አለቃ ሲሳይ፤ ብሔርን መሰረት ያደረጉ ጭፍጨፋዎችን መፈጸሙና አጎራባች ክልሎችን መውረሩ በአለም አቀፍ ደረጃ በሽብር ቡድንነት እንዲፈረጅ በቂ ምክንያት መሆኑንም አመላክተዋል።
የአሜሪካ መንግስት የአሸባሪውን ቡድን እኩይ ተግባር ወደ ጎን ከመተው ባለፈ የኢትዮጵያን እውነታ ከግምት ውስጥ ያላስገባ ተጨማሪ ማዕቀብ ለመጣል መነሳሳት ተገቢነት እንደሌለው ገልጸዋል።
ለውጭ ጫናዎች ባለመንበርከክ አሸባሪውን ቡድን ለማጥፋት ጥረታችንን በቅንጀት አጠናክረን መቀጠል አለብን።
የአሜሪካን መንግስት ማዕቀብ ለመጣል መጣር የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ለሰላም የሰጡትን ዋጋና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በማጣራት እርምጃ ለመውሰድ የሚያደርጉትን ጥረት ከግምት ውስጥ ያላስገባ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በወናጎ ከተማ በንግድ ዘርፍ የተሰማሩት አቶ መሐመድ ሁሴን ናቸው።
ይህም የኢትዮጵያን መንግስት ከአሸባሪው ቡድን እኩል እውቅና የሰጠ በመሆኑ ፍትሃዊት የጎደለው ነው ያሉት።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ለመጣል ያላቸውን አቋም በፊርማቸው ማንጸባረቃቸው ይታወቃል።