በኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ የተሰየመው አደባባይ ሊመረቅ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ የተሰየመው አደባባይ ሊመረቅ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ አዲስ አበባ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የተሰየመው አደባባይ የፊታችን እሁድ ይመረቃል።
የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌደሬሽንና የለሚ ኩራ ክፍል ከተማ የፊታችን እሁድ የሚመረቀውና በኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ የሚሰየመውን አደባባይ በማስመልከት በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በአፍሪካ የመጀመሪያዋ ጥቁር አፍሪካዊት ሴት የኦሊምፒክ ባለድል በመሆን የበርካታ አትሌቶች የጀግንነት ምሳሌ አደባባይ መሰየሙ እንደሚያስደስታቸው ገልጸዋል።
የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አሊያስ ሙሀመድ፤ በጀግናዋ አትሌት ስም በክፍለ ከተማችን አደባባይ በመሰየሙ እንኮራለን ብለዋል።
እንደ ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ አይነት ዓለም አቀፍ ጀግኖችን ማክበር ሌሎች ጀግኖችንም ለማፍራት ያግዛል ብለዋል።
በመሆኑም በጀግናዋ አትሌት ደራርቱ ቱሉ ስም የተሰየመው አያት የሚገኘው አደባባይ የፊታችን እሁድ በይፋ ይመረቃል ብለዋል።
በኮማንደር አትሌት ደራርቱ ተሉ እኤአ በ1992 የባርሴሌና ኦሊምፒከም በ10 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ በማምጣት ለሴት ጥቁር አፍሪካዊያን ፈር ቀዳጅ አትሌት ናት።
በሲዲኒ ኦሊምፒክም ለኢትዮጵያ ወርቅ አምጥታለች፤ ከዚህም ባለፈ በርካታ ድሎችን በማስመዝገብ ስሟ በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ ይጠራል።
በኮማንደር ኮሎኔል ደራርቱ ተሉ አሁን ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን በፕሬዚዳንትነት እየመራች ትገኛለች።
በእለቱ ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ለማድረግ ዓላማ ያደረገ የ5 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ይካሄዳል ተብሏል።
አደባባዩን በኦሊምፒክ አርማ የማስዋብና አረንጓዴ የማድረግ ስራዎች ተከናውኗል ያሉት ደግሞ የክፍለ ከተማው ስፖርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አበበ አንሙት ናቸው።
በእለቱ ለሚካሄደው የ5 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር የተለያዩ ዝግጅት ተደርጓል፤ የመወዳደሪያ ማሊያውም በክፍለ ከተማው ሁሉም ወረዳዎች ይገኛል ብለዋል።