የወጣቶችና ሴቶች ሊግ ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
የወጣቶችና ሴቶች ሊግ ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 10/2014 (ኢዜአ) የወጣቶችና ሴቶች ሊግ በወሎ ግንባር በመገኘት ለጸጥታ ኃይሎችና በደሴ ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከ19 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብ፣ አልባሳትና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ።
ድጋፉ የተደረገው በወሎና አፋር ግንባር እየተፋለመ ለሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች እንድሁም ለተፈናቃይ ወገኖች ነው።
የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ኃላፊ አቶ አክሊሉ ታደሰ በበኩላቸው በየዘመናቱ ኢትዮጵያን ለመድፈር የመጡ ጠላቶች ሽንፈትን ተከናንበው መመለሳቸውን አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን የደፈረ ጠላትን እንዴት ተባብረው ማሸነፍ እንደሚችሉ ያቁበታል ያሉት አቶ አክሊሉ፤ ድጋፉ ይህንኑ የሚያረጋግጥ መሆኑን ተናግረዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ኃላፊ መስከረም አበበ፤ የብልጽግና ፓርቲ የሴቶችና ወጣቶች ሊግ በጋራ በመሆን በወሎ ግንባር ለሚፋለሙ የጸጥታ አካላትና በአሸባሪ ቡድኑ ወረራ ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ19 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የምግብና አልባሳት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ወጣቶችና ሴቶች ሊግ በጋራ በመሆን በአጠቃላይ በወሎና አፋር ግንባር ለሚገኙ ዜጎችና የጸጥታ አካላት ከ38 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ሃብት ማሰባሰባቸውንም ጠቁመዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሳይ ማሩ፤ በአሸባሪው የህወሃት ወራሪ ኃይል ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
የወጣቶችና ሴቶች ሊግ በጋራ በመሆን ላደረጉት ሰብዓዊ ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።
የወሎ ግንባር የኢንዶክትሪኔሽን ዳይሬክተር ተወካይ ሌተናል ኮሎኔል ለቺሳ መገርሳ ድጋፉ አሸባሪውን የህወሃት ቡድን በአጠረ ጊዜ ለማጥፋት ለሠራዊቱ የሞራል ስንቅ ይሆናል ብለዋል።
ወጣቶች አካባቢያቸውን ነቅተው እንዲጠብቁም ነው ያሳሰቡት።
የወጣቶችና ሴቶች ሊግ የህልውና ዘመቻ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።