የሞጆ - መቂ - ባቱ የክፍያ የፍጥነት መንገድ አገልግሎት መስጠት ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የሞጆ - መቂ - ባቱ የክፍያ የፍጥነት መንገድ አገልግሎት መስጠት ጀመረ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሞጆ - መቂ - ባቱ የክፍያ የፍጥነት መንገድ ግንባታ ተጠናቅቆ ዛሬ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል። መንገዱ በ6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ወጪ መገንባቱም ተገልጿል።
የፍጥነት መንገዱ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ይፋ በሆነበት መርሃ ግብር የትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለልጣን እና የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።
ከዛሬ ጀምሮ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የሞጆ-መቂ- ባቱ የክፍያ መንገድ ከአዲስ አበባ አዳማ እና ድሬዳዋ ደወሌ ቀጥሎ ሶስተኛው የክፍያ መንገድ ነው።
92 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና 32 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን አምስት ደረጃቸውን የጠበቁ የክፍያ ጣቢያዎች አሉት።
የክፍያ ጣቢያዎቹ ሞጆ፣ ቦቴ፣ ቆቃ፣ መቂ እና ባቱ መውጫ ጣቢያዎች ናቸው።
የክፍያ መንገዱ በ6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የተገነባ ሲሆን ወጪው ከኮርያ ኤግዚም እና ከልማት ባንክ በተገኘ ብድር እንዲሁም በኢትዮጵያ መንግስት መሸፈኑ ተገልጿል።
የክፍያ መንገዱ የአዲስ አበባ-አዳማ-ሞያሌ-ሞምባሳ የመንገድ ኮሪደር አካል ሲሆን፤ የአፍሪካ የክፍያ መንገድ የሚገኙ አገራትን የሚያገናኝ እንደሆነም ተነግሯል።
የሞጆ-መቂ-ባቱ የክፍያ የፍጥነት መንገድ ግንባታ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መመረቁ ይታወቃል።